የወንጌል ማዕከላዊነት፦ ማስጠንቀቂያ እና ምክር

ወንጌልን ሳንለቅ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ላይ እንዴት መሥራት እንችላለን? በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ወንጌል ብቸኛ አስፈላጊ ነገር ከሆነ ከወንጌል አልፈን ሌሎች ነገሮች ላይ መሥራት በመርሕ ደረጃ ልክ ሊሆን ይችላልን?

እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ስለ ወንጌል ማዕከላዊነት በወንጌላውያን አማኞች መካከል በዋነኝነት የሚጠየቁ ጥያቄዎች ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ሁለት በወንጌል ማዕከላዊነት እንቅስቃሴ ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ተመልክቼ ነበር። በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ለመዳሰስ እሞክራለሁ፤ አንዱ ምክር አዘል ሐሳብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማስጠንቀቂያ ነው።

በመጀመሪያ በወንጌላውያን መካከል የሚታየውን ለወንጌል ትኩረት የመስጠት አካሄድ በጣም የሚደነቅና ማመሥገን የምፈልገው ነው። ወንጌል ለቅድስናችን ማዕከል መሆኑ ማለትም በቃሉ እንድንታዘዝ የተቀመጡልን ነገሮች ከተደረጉልን ነገሮች የሚነሡ መሆናቸውና ከወንጌል አልፈን መሄድ ሳይሆን ወደ ወንጌል በጥልቀት ዘልቀን መግባት እንዳለብን የሚነግሩን ድምፆች ትክክል ናቸው። እነዚህ ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መከራከሪያ ነጥቦች ናቸው።

ሁለት የወንጌላውያን አመለካከቶች፦ መሠረታውያን (ESSENTIALISM) እና መሠረታዊያን ያልሆኑ(REDUCTIONISM)

አንድ ሰው፣ “ወንጌል ብቸኛ አስፈላጊ ነገር ከሆነ፣ ወደ ሌላ የትኛውም ነገር መሄድ እንችላለን ወይ?” ብሎ ሊጠይቅ ይችላል።

ወንጌላውያን ከሥር መሠረቱ መሠረታውያን ነን። በብዙ ታሪካዊ ምክንያቶች የተነሣ ሕይወታችንን በተወሰኑ መሠረታዊ ነገሮች ነው ምንመራው። ብዙ ጊዜ ሲወራ እንደምሰማው ሁለት ማርሽ ነው ያለን፤ ይኸውም መሠረታዊ ነገሮች እና ያን ያህል መሠረታዊ ያልሆኑ ነገሮች ናቸው።

በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ አስጊው ነገር ወንጌል አስፈላጊ ወይም መሠረታዊ የሚለውን ቦታ ከያዘ (በርግጥም መያዝ አለበት!) ቀሪዎቹ ነገሮች ሁሉ ተሰብስበው አላስፈላጊ የሚል ቅርጫት ውስጥ ይገባሉ።

በሕይወታችንና በአገልግሎታችን ወንጌልን ምንም ነገር ሊጋርደው፣ ሊያደበዝዘው ወይም ጥግ ሊያስይዘው አይገባም በሚሉ ሐሳቦች ውስጥ አንዳንዴ ከላይ ያነሣሁትን ሥጋት በጨረፍታ አይበታለሁ። እንደዚህ ዐይነት ማስጠንቀቂያዎች አስፈላጊም ልክም ናቸው፤ ነገር ግን በመሠረታዊ ነገሮችና መሠረታዊ ባልሆኑ ነገሮች መካከል ሌላ አንድ ደርዝ ካልፈጠርን ወንጌላችን ራሱ አደጋ ውስጥ መሆኑ አይቀሬ ነው። ወንጌልን ወንጌል ላይ ብቻ በማተኮር ጠብቆ ማቆየት አይቻልም። ብንረሳቸውና ብንተዋቸው መጥፊያችን የሆኑ ወንጌልን ጠብቆ ለማቆየት ወሳኝ የሆኑ እግዚአብሔር የሰጠን አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች አሉ።

ለምሳሌ የሥላሴን አስተምህሮ ከወንጌል ነጥሎ መመልከት አይቻልም። አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በድነት አኳያ የተለያየ ሚና አላቸው፤ ስለዚህም የትኛውንም የሥላሴ አስተምህሮ መበረዝ፣ ወንጌልን መበረዝ ይሆናል።

ሌላ ምሳሌ ልጨምር፦ የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛነት ለወንጌል የማይነቃነቅ ሥነ ዕውቀታዊ (ኢፒስቲሞሎጂካል) መሠረት ይሰጠናል። ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቃል እውነተኝነትና ታማኝነት ላይ ነው።

ወንጌልን ጠብቀው የሚያቆዩልን ሥርዐቶች ጋር ደግሞ ስንመጣ የቤተ ክርስቲያን አባልነትንና የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽን መውሰድ እንችላለን። ጆናታን ሊማን እንዳለው፣ የቤተ ክርስቲያን አባልነት በዓለም ውስጥ ማን ክርስቶስን ወክሎ እንደሚንቀሳቀስ ሲያሳየን፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ደግሞ የኢየሱስ ስም በዓለም እንዳይሰደብ ይከላከልልናል።

የቤተ ክርስቲያን አባልነት የትኞቹ ሰዎች የወንጌል አባል እንደ ሆኑ ይለይልናል። የቤተ ክርስቲያን አባልነት ለዓለም “ወንጌል የፈጠራቸው አዲስ ማኅበረ ሰብና የወንጌሉ ሰዎች” እነዚህ ናቸው ብሎ ይናገራል።

የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም የምታሳየውን የወንጌልን መልክ ጠብቆ ያቆይልናል። ቤተ ክርስቲያንን ለሚመለከታት ዓለም የተሳሳተ የወንጌልን ሥዕል ከመስጠት ይታደጋታል። ይህን የሚያደርገውም ክርስቲያን መሆን ምን ማለት አይደለም የሚለውን በማሳየት ነው፤ ማለትም “ይህ ሕይወት ወይም ኑሮ ከወንጌል የሚመነጭ አይደለም” በማለት ነው።

ሲቀጥልም አንድ ሰው እንደ ተናገረው፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ወንጌል በድርጊት ሲገለጥ ማለት ነው። በክርስቶስ ውስጥ ከሆንን እግዚአብሔር በኀጢአት ውስጥ ጥሎን አይሄድም። እኛም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባሎችን በኀጢአት ውስጥ ጥለናቸው መሄድ የለብንም። በተቃራኒው ወደ እነርሱ ተጠግተን በፍቅር የሆነ ተግሣጽንና የክርስቶስን ነፃ ይቅርታ መስጠት አለብን።

እነዚህ አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች እንዲሁም ሌሎች እነዚህን የመሰሉ ብዙዎቹ ከወንጌል ጋር የተቆራኙ ናቸው። ግንኙነታቸው ተፈጥሮአዊ ነው። እነዚህን ወደ ጎን ገሸሽ ካዳረግናቸው የወንጌል ምስክርነታችንና የወንጌል አረዳዳችን ላይ ትልቅ ጉዳት እናደርሳለን።

ስለዚህ ማስጠንቀቂያዬ የወንጌል ማዕከላዊነት ብቻ ነው አስፈላጊው ነገር ወደሚል መሠረታዊነት ከዚያም ቀጥሎ ብዙ ነገር ወደሚያስወግድ ወደ ቀናሽነት አመለካከት እንዳንወሰድ ነው። እውነት ነው፤ ወንጌልን የሕይወታችን ማዕከልና የቤተ ክርስቲያናችን ማዕከል ማድረግ ልክ ነው። ነገር ግን ግድ የሚለን አንድና ብቸኛ ነገር “ወንጌል ብቻ” ነው ማለት ልክ አይደለም።

ነጥቦቹን ማገናኘት

ከላይ መጀመሪያ ላይ ያነሣነውን ጥያቄ ማለትም ወንጌልን ሳንለቅ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ላይ እንዴት መሥራት እንችላለን? የሚለውን እንይ። ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ወንጌልን ሳንለቅ እንዴት ከላይ ያነሣናቸውን አስተምህሮዎች እናስተምር? እንዴትስ እነዚህን ሥርዐቶች እንለማመድ? ማለት ነው።

የኔ ምክር፦ ይህን ማድረግ የምንችለው ያለመታከት እነዚህን አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች ከወንጌል ጋር በማገናኘት ነው።

ይህንን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከላይ አሳይተናል። ትምህርተ ሥላሴ፣ የቃለ እግዚአብሔር ሥልጣን፣ የቤተ ክርስቲያን አባልነት፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ እንዲሁም ብዙ አስፈላጊ አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች ከወንጌል ጋር ተፈጥሮዊ ግንኙነት አላቸው።

አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ወንጌልን ሳይለቅ እነዚህ አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች ጋር መሄድ ከፈለገ፣ መንገዱ ከወንጌል ጋር ያላቸውን ተፈጥሮዊ ግንኙነት ግልጽ በሆነ መንገድ በስብከቱና በትምህርቱ ማሳየት ነው። ከወንጌል ላይ ትኩረታችንን ሳናነሣ ወደ ሌሎች ነገሮች የመሄጃው መንገድ ከወንጌል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማሳየት ነው።

ስለዚህ ወንጌልን መሠረት በማድረግ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌነት፣ ስለ ልጆች አስተዳደግ፣ ስለ መጨረሻው ዘመን፣ የፍቅር ጓደኛ አፈላለግ፣ ስለ ጥምቀት ወዘተ… አስተምሩ፤ ነገር ግን ይህን ስናደርግ እያንዳንዱ ነገር ከወንጌል ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ማሳየት አለብን። በዚህ መንገድ ከሄድን እነዚህ አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች ከወንጌል ጋር ውድድር ውስጥ አይገቡም፤ እንዲያውም እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሄዳሉ እንጂ።

የወንጌል ማዕከላዊነታችሁ የወንጌል ቅነሳ እንዳይሆንባችሁ። ይልቁንም ሁሉንም ነገሮች ከወንጌል ጋር ያላቸውን ግንኙነታቸውን አሳዩ፤ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና የማኅበር ሕይወታችንን ጨምሮ።

ቦቢ ጀምስ