ለምንኖርበት ማኅበረሰብ ወንጌልን መስበክ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ክርስቲያኖችን ለማሳመን ብዙም ጥረት አያስፈልግም። እንዲያውም አንድ የመንፈሳዊ ኮንፍረንስ ሥራ ላይ ተሳታፊ ሰዎችን ማግኘት ከባድ ነገር አይደለም።
ነገር ግን፣ ብዙ ጊዜ ወንጌልን ለማኅበረሰባችን መስበክ ስናስብ ወደ ምናባችን የሚመጣው የመንፈሳዊ ኮንፍረንስ ወይም የወንጌል ስብከት ፕሮግራም ነው፤ ሆኖም ግን ወንጌልን መስበክ እና የወንጌል ስብከት ፕሮግራም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። “ፕሮግራም” ወይም “ኮንፍረንስ” ስል አንድ ታዋቂ ሰው የሚናገርበት፣ ወይም አስደሳች የሆነ ርእስ ያለው ትልቅ ዝግጅትን ማለቴ ነው። በዝግጅቱ መካከል ወንጌሉ የሚነገርበት የሆነ ሰዓት አለ። ወይም ደግሞ ፕሮግራሙ በማያስታውቅ መንገድ የሆኑ ሰዎችን ለመድረስ የተዘጋጀ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ለወንጌል ስብከት ወይም ለመንፈሳዊ ንግግሮች በር ይከፍታል ተብሎ የሚታሰብ አንድ ፕሮጀክት ወይም የስፖርት ፕሮግራም ይኖራል።
እግዚአብሔር ፕሮግራሞችን ሊጠቀም ይችላል። የወንጌል ስብከት ኮንፍረንሶች ላይ ተገኝተው ወደ እምነት የመጡ የማውቃቸው ሰዎች አሉ። እኔም ራሴ ወንጌልን መሠረት ያደረጉ ፕሮግራሞችን አስተዋውቃለሁ፤ እንዲሁም እነዚህ ኮንፍረንሶች ላይም እንድናገር እጋበዛለሁ። ነገር ግን፣ ኮንፍረንሶች ውጤታማ እንዲያውም ዋነኛው የወንጌል መመስከሪያ መንገድ ናቸው ብዬ አላስብም።
ስለዚህ በደንብ አጢናችሁ ፕሮግራሞችን ብትመለከቷቸው፣ ችግሮቹን ልታስተውሉ ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ለፕሮግራሞች የሚወጣው ገንዘብ፣ በአንጻሩ በወንጌል ስብከት ከሚገኘው ፍሬ ያነሰ ነው። ለምሳሌ ከ21 ዓመት በታች ያሉ ሰዎች (ብዙ ሰው ወደ እምነት የሚመጣበት የእድሜ ክልል) እንዴት ወደ እምነት እንደመጡ ተጠይቀው፣ በቲቪ ወይም በሌላ ሚዲያ ምክንያት 1% ብቻ ሲሆኑ አብላጫው 43% የሚሆኑት ደግሞ ወደ እምነት የመጡት በጓደኛ ወይም በቤተሰብ አባል አማካኝነት እንደሆነ ተናግረዋል። በአንድ ሲኒ ቡና እና በቲቪ ፕሮግራም መካከል ያለውን ወጪ እስቲ አነጻጽሩት። ወይም ደግሞ ውጤቱን እንዲህ ብላችሁ አስቡት፤ ከፕሮግራሞች በተሻለ እናቶች ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይመራሉ።
የሚገርመው ወንጌልን መሠረት ያደረጉ ፕሮግራሞች ከወንጌል ምስክርነት ይልቅ በተሻለ የክርስቲያን ማኅበረሰብን ለመፍጠርና አማኞችን ለክርስቶስ ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው ለማበረታታትና እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎችን ለማስጀመር ያስችላሉ።
ቢሆንም ግን የወንጌል ስብከትን በፕሮግራሞች ለማሳካት የሚያስብ በውስጣችን ያለ የማይረካ ረሃብ አለ። ለምን? ፕሮግራሞች ልክ እንደ ስኳር ናቸው። በጣም ይጣፍጣሉ፣ ሱስ እስከመሆንም ሊደርሱ ይችላል። ነገር ግን ለጤናማ ምግብ ያለንን ፍላጎት ያጠፋል። ምንም እንኳን ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ኅይልን ቢሰጥም በኋላ ግን ልፍስፍስ ያደርጋል፤ ቋሚ ምግብ ቢደረግ ደግሞ ይገድላል።
የወንጌል ስብከት ፕሮግራሞች ላይ ብቻ ማተኮር የቀጨጨ የወንጌል ስብከትን ያስከትላል። ልክ ስኳርን ስንመገብ ሳንበላ የመጥገብ ስሜት እንደሚፈጥርብን ሁሉ፣ ፕሮግራሞችም ብዙ ጊዜ የወንጌል ምስክርነትን ሳንሠራ እንደሠራን እንድናስብ ያደርጉናል። ስለዚህ ፕሮግራሞችን በተመለከተ ጤናማ የሆነ ጥርጣሬ ሊኖረን ይገባል። እግዚአብሔር ዝግጅትን ሳይሆን ልጁን እንደላክ እያስታወስን በመጠኑ እና በዘዴ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
ታዲያ ምን እናድርግ? ወንጌልን ለማኅበረሰብ መመስከር እንፈልጋለን። እምነታችንን ለሌሎች ስናካፍል ጓደኞቻችን ከጎናችን እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ነገር ግን በዚያው ልክ የፕሮግራሞችን ውሱንነት እንዲሁም አደጋዎችን እናያለን። ሌላ አማራጭ ይኖር ይሆን?
አንድ ከዚህ አካሄድ በጣም የተለየ ማኅበራዊና ግለሰባዊ አካሄድ ለመጠቆም እፈልጋለሁ። ይህም ልምምድ አባል በሆንባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚኖር ወንጌልን በመመስከር ላይ ያተኮረ ባህል ወይም ልምድ ነው።
ቤተ ክርስቲያን እና የወንጌል ምስክርነት
ኢየሱስም አለ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” (ዮሐንስ 13፥35)። ከዚያም ከደቀመዛሙርቱ ጋር ትንሽ ቆይቶ አንድ እንዲሆኑ ጸለየ፦ “እንዲሁም አንተ እኔን እንደላከኝ ዓለም ያምን ዘንድ” (ዮሐንስ 17፥20-21)። በእውነት የመዳናችን መገለጫው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳችን ለሌላችን ያለን ፍቅር መሆኑን ኢየሱስ እየነገረን እንደሆነ መረዳት አለባችሁ። በእውነት የመዳናችን መግለጫው በአካሉ ውስጥ አንድ ስንሆን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለዓለም እናሳያለን። ፍቅር ደቀ መዝሙርነታችንን ያረጋግጣል። አንድነት የክርስቶስን አምላክነት ያረጋግጣል። እንዴት ያለ ኅይለኛ ምስክርነት ነው!
የወንጌል ምስክርነት ጥረታችንን የሚመሩ እና ቅርጽ የሚያስይዙ ሌላ ብዙ ክፍሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ። ነገር ግን ከላይ ያሉት ጥቅሶች ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ምስክርነት ባህል ማሳያ ለመሆኗ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ናቸው።
ይህ ማለት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ወንጌልን በግልጽ ማሳያ ናት ማለት ነው። ወንጌልን እርስ በርሳችን ባለን ፍቅር ማሳየት ያለብን ከሆነ፣ ያ ሊሆን የሚችለው በፍቅር ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በኪዳን በተሳሰሩ የአጥቢያ ምእመናን መካከል ነው። ይህ ረቂቅ ወይም የማይጨበጥ ፍቅር ሳይሆን፣ በእውነተኛው ዓለም ውስጥ ላሉ እውነተኛ ሰዎች መካከል ያለ ፍቅር ነው። ክርስቲያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች እንዴት ቤተ ክርስቲያን ለእነርሱ እንግዳ እንደሚሆንባቸው ነገረውኝ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ወደዚያ ሕብረት የሳባቸው በአባላቱ መካከል ያዩት ልዩ ፍቅር ነው።
ይህ ማለት ግን ወንጌል በፍቅራችን ብቻ ነው የሚገለጠው ማለት አይደለም፡፡ በትክክል ቢተገበሩ የወንጌል አዋጅ የሚሆኑ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደረጋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ስንት እንደሆኑ አስባችሁ ታውቃላችሁ?
ጤናማ የወንጌል ምስክርነት ባህልን አጥብቀን ለመከተል በመሞከር፣ ቤተ ክርስቲያንን እንደ አዲስ ለወንጌል ስብከት አንሠራትም። እንዲያውም ወንጌልን ለማወጅ እግዚአብሔር አሰቀድሞ በቤተ ክርስቲያን የመሠረታቸውን ሥርዐቶች እንፈጽማለን። ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን በመሠረተ ጊዜ ወንጌልን አልረሳም።
ለምሳሌ፣ ጥምቀት የኢየሱስን ሞት፣ መቀበር እና ትንሣኤን ይወክላል። የእርሱ ሞት የእኛም ሞት እንደሆነና ሕይወቱም ሕይወታችን እንደሆነ ያሳያል። የጌታ እራት እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ የክርስቶስን ሞት ያውጃል፤ እኛንም ኅጢአታችንን እንድንናዘዝና የኃጢአት ይቅርታን እንድንለማመድ ያደርጋል። ስንጸልይ የእግዚአብሔርን እውነታዎች እንጸልያልን። ስንዘምር እግዚአብሔር በወንጌሉ በኩል ያደረገልንን ታላቅ ነገሮች እንዘምራለን። ገንዘባችንን በመስጠት ደግሞ የወንጌልን መልእክት ለማዳረስ እንረዳለን። በዋናነት ደግሞ የቃሉ ስብከት ወንጌልን ያመጣል።
በእውነቱ ከሆነ መጀመሪያውኑም ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው የቃሉ ስብከት ነው። አንዴ ከተመሠረተች በኋላ ሌሎች ደቀ መዛሙርትን የማፍራት ሥራ ይሰጣታል፤ እነዚያም ደቀ መዛሙርት ተልከው ወንጌልን በመስበክ ሌላ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ይመሠርታሉ። ይህ ዑደት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ ዳግም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።
የወንጌል ምስክርነት ባህል ከላይ ወደታች የሚወርድ ሳይሆን ከሥር ጀምሮ ያለ ነው።
በወንጌል ምስክርነት ባህል ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራ፣ ቤተ ክርስቲያን መሆን እንደሆነ ሰዎች ይረዳሉ። የቤተ ክርስቲያን ሥርአቶች ራሳቸውን የቻሉ መመስከሪያዎች ናቸው። በርግጥም ደግሞ ቤተክርስቲያን የወንጌል ሥርጭቶችን በጸሎት እና በሌሎች መንገዶች ትደግፋለች። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ሚና ፕሮግራሞችን ወይም ኮንፈረንሶችን ማስፈጸም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ምስክርነት ባህልን ማዳበር አለባት። ወንጌልን ለመስበክ የሚላኩት የቤተ ክርስቲያን አባላት በሙሉ ናቸው። በርግጥ ይህ ማማረጥ ሊመስል ይችላል፤ ግን እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። እዚህ ነጥብ ላይ ከሳታችሁ፣ የቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ በተሳሳተ መልኩ በመቆጣት ቤተ ክርስቲያንን ልታቃውሱ ትችላለችሁ።
ስለዚህ ጤናማ በሆነ የወንጌል ምስክርነት ባህል ውስጥ ለግለሰብ እና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ቅድሚያ የተለያየ እንደሆነ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ወንጌልን የምትኖር ቤተ ክርስቲያን እና ስለማያምኑ ሰዎች ግድ የሚላቸው ክርስቲያኖች ያስፈልጉናል። ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን የምትኖር፣ አማኞች ደግሞ ሰው ፈላጊ ሊሆኑ ይገባል እንጂ የተገላቢጦሽ መሆን የለበትም፡፡ ይህም ማለት በግላችሁ ወንጌልን ለመስበክ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ እንደ ማህበር ማድረግ ያለባት ነገር ላይሆን ይችላል ማለት ነው።
የወንጌል ምስክርነት ባህል ዋና ግቡ፣ ከመጋቢውና ሽማግሌዎቹ ባሻገር ሁሉም ክርስቲያን በወንጌል ሥራ ውስጥ እንዲካፈል፣ እንዲጸልይ እና የሚገኙትን አጋጣሚዎች እንዲጠቀም ማድረግ ነው። የእኛ ኅላፊነት አብረን ታማኝ ምስክሮች መሆን ነው።
የቤተ ክርስቲያን አባላት ፕሮግራሞች ላይ ከሚያጠፉት ጊዜ ግማሹን እንኳን ለጓደኞቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እና አብረዋቸው ለሚማሩ ወንጌልን በመስበክ ቢጠመዱ ብዙ ሰዎችን በወንጌል ከመድረሳቸውም ባሻገር የተሻለ ምላሽ ያገኛሉ።
የቤተ ክርስቲያናችሁ አዳራሽ ምንም ያህል ትልቅ ቢሆን፣ እያንዳንዱ አባል በሳምንት ውስጥ የሚያገኛቸውን ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ ሊያካትት አይችልም። ስለዚህም በስንት አንዴ ከሚደረግ የወንጌል ስብከት ፕሮግራም ይልቅ፣ እያንዳንዱ አባል በዙሪያው ላሉ ሰዎች ሁሉ ወንጌልን እየነገረ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጋበዝ ባህልን ቢያዳብር እጅግ የተሻለ ሥራ መሥራት ይቻላል።
እውነታው ይህ ነው፤ በርካታ ሰዎች ወደ ክርስትና የሚመጡት በቤተሰብ አባል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖች፣ ወይም ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኋላ ከጓደኛ ጋር በሚደረግ ንግግር ተጽእኖ አማካኝነት ነው። ክርስቲያኖች ሆነ ብለው ስለ ወንጌል በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ በመናገራቸው ነው።
በጄ. ማክ. ስቲልስ
የአርታዒ ማስታወሻ፦ ይህ መጣጥፍ፣ ጤነኛ አብያተ ክርስቲያናትን መገንባት መድብል ውስጥ ከሆነው እና በቅርቡ ከወጣው “የወንጌል ስብከት፦ መላ ምዕመኑ ስለ ኢየሱስ እንዴት ይናገሩ” ከሚለው መጽሐፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው። ከሦስት ቅንጭቦች የመጨረሻው ነው (የመጀመሪያው፣ “ወንጌል ስብከትን እንዴት እንተርጉመው?” የሚል ሲሆን እዚህ ያገኙታል። ሁለተኛው፣ “ትርጉሞች፦ ወንጌል እና ማሳደድ” የሚለውን እዚህ ያገኙታል።)