ታላቁ ተልእኮ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ምን ይፈልጋል?

ኢየሱስ፣ ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ያዘዘውን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ (ማቴዎስ 28፥19) አብያተ ክርስቲያናት፦

  1.  ያለማቋረጥ ወንጌልን ሊሰብኩ ይገባል። ቤተ ክርስቲያን ዓለምን መስበክ ከፈለገች፣ ጎረቤቶቿን በመስበክ መጀመር አለባት። የመጀመሪያው እርምጃ፣ በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ይፋዊ አገልግሎት ወንጌልን በግልጽ መስበክ ነው።
  2. ሰዎች ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲታዘዙ ማስተማር አለባቸው። ታላቁ ተልእኮ ኢየሱስን የሚከተሉ፣ የሚመስሉ እና የሚታዘዙ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ትእዛዝ ነው። በማደግ ላይ ያሉ ደቀ መዛሙርት የተሻሉ ምስክሮች ይሆናሉ።
  3. እያንዳንዱ አባል በግልጽ ወንጌልን እንዲሰብክ ማስታጠቅ አለባቸው። ፓስተሩ ብቸኛው ወንጌላዊ ሊሆን አይችልም። ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም አባሎቿን በስብከተ ወንጌል ማሠልጠንና ማበረታታት አለባት። የወንጌል ስብከትን የሚያስተምር የሰንበት ትምህርት ቤትን አጥብቃ መያዝ። ለግል ምስክርነት አገልግሎት የሚውል የወንጌል ትምህርትን ማዘጋጀት። ለስብከተ ወንጌል ጥረት ከቤተ ክርስቲያን ጋር ዘወትር መጸለይ።
  4. በሌሎች አገሮች ካሉ ሚስዮናውያን ጋር ለመተባበር ዕድሎችን ይፈልጉ። አብያተ ክርስቲያናት ወንጌልን ለጎረቤቶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ክርስቶስ የማይታወቅባቸው ስፍራዎችም ጋር ለማድረስ መጣር አለባቸው (ሮሜ 15፥20)። ስለዚህ በሌላ አገር እየደከሙ ካሉ፣ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር አጋርነት ፈልጉ።

ወንጌልን ለሌሎች አገራት የሚያደርሱ አባላትን እግዚአብሔር እንዲያስነሣ መጸለይ አለባቸው። የእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ የተለየ ይሆናል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን፣ እግዚአብሔር ለሚሲዮናዊ አገልግሎት የሚተጉ የራሱ ሰዎችን እንዲያስነሣ መጸለይ አለባት።