አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም በመደበኛነት ተሰባስበው፣ በወንጌል ስብከት እና በወንጌል በተደነገጉ ሥርዐቶች በኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንግሥቱ ያላቸውን ሕብረት በይፋ የሚያጸኑበት እና እርስ በእርስ የሚተያዩበት ስብስብ ነው። ይህ ትርጉም የተንዛዛ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ነገር ግን ይህ ትርጉም ውስጥ አምስት ክፍሎች እንዳሉት ልብ በሉ፦
• የክርስቲያኖች ስብስብ
• መደበኛ ስብሰባ
• በመላ ጉባኤው የሚደረግ፣ እርስ በእርስ የመጽናናት እና የመተያየት ተግባር
• ክርስቶስን እና የእርሱን የምድር ግዛት በይፋ የመወከል ዓላማ (በስሙ በመሰብሰብ)
• በወንጌል ስብከት እና በወንጌል በተደነገጉ ሥርዓቶች ይህንን ዓላማ ማስፈጸም
የቤተ ክርሰትያን መጋቢ ሊጋቡ የመጡ ወንድና ሴትን እንደተጋቡ ሲያውጅ ባልና ሚስት እንደሚሆኑ ሁሉ፣ ከላይ የተዘረዘሩት የመጨረሻዎቹ አራት ነጥቦች፣ በመናፈሻ የሚደረግን ተራ የክርስትያኖች ስብስብ እነሆ! ወደ አጥብያ ቤተ ክርስትያንነት ይለውጣታል።
ስብስቡ በብዙ ምክንያቶች ጠቃሚ ነው። አንደኛ፣ እንደ ክርስትያን ትልቁ ውግንናችንን በአደባባይ የምናውጅበት ቦታ ነው። ቆንስላ[1] ነው፤ ማለትም የሚመጣው መንግሥት ገጽታ ነው። በንጉሣችን ፊት የምንሰግድበት ቦታም ነው፤ ይህንንም አምልኮ ብለን እንጠራዋለን። የዓለም ፈርዖኖች ቢቃወሙንም እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን ከአሕዛብ መካከል እንዲያመልኩት ይጠራል። እግዚአብሔር ታላቅ ጉባኤውንም ይሠራል።
ንጉሣችን ሕግጋቱን በስብከት፣ በወንጌል በተደነገጉ ሥርዓቶች እና ሥነ ሥርዐት ምክንያት የሚፈጽመውም በስብሰባችን ውስጥ ነው። የወንጌል ስብከቱ የመንግሥታችንን ሕግ ያብራራል። የንጉሣችንን ስም ያውጃል፤ ንጉሣችን ለመሆን የከፈለውን መሥዋዕትነትም ያብራራል። መንገዱን እያስተማረን፣ አለመታዘዛችንን ይጋፈጣል። የእርሱን በቶሎ መምጣትም ያረጋግጥልናል።
በጥምቀት እና በጌታ እራት ሥነ ሥርዐት በኩል ቤተ ክርሰትያን የመንግሥታችንን ባንዲራ ታውለበልባለች፤ ሠራዊቱንም ታስታጥቃለች። መጠመቅ ማለት ራሳችንን ከአብ፣ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕብረት እንዳለን መመስከር ነው፤ እንዲሁም ከክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ጋር አንድ የምንሆንበት መንገድ ነው (ማቴዎስ 28፥19፤ ሮሜ 6፥3-5)። የጌታን ራት በምንወስድበት ጊዜ፣ የክርስቶስን ሞት እና የአካሉም አባል መሆናችንን እናውጃለን። እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲታወቅለት እና እንዲለይለት ይፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መካከል ግልጽ መስመር እንዲኖር ይፈልጋል። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወንጌል እንዲሰበክ፣ ወንጌል መስካሪዎችን ሊያጸና፣ ደቀ መዝሙራትንም ሊመለከት እና አስመሳዮችን ሊያጋልጥ የፈጠራት፣ ሥልጣን የሰጣት ተቋም ነች። ይህ ማለት ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ተራ ቡድን አንቀላቀላትም፤ ይልቅ እንገዛላታለን።
በጆናታን ሊማን
[1] ኤምባሲ