በቀብር ሥነ ሥርዐት  ላይ ወንጌልን እንዴት እንስበክ?

“ወደ ገነት አልያም ወደ ሲኦል እየጠቆምክ አትስበካቸው። ነገር ግን ለታዳሚዎቹ ወንጌሉን ብቻ ስበክ።” ይህ በማላውቀው ሰው የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ስለ መስበክ ያገኘሁት ጠቃሚ ምክር ነው። የቀብር ሥነ ሥርዐታችን ምንም ዐይነት ቢሆን፣ ይህ ለተግባራችን ወሳኝ መርሕ ነው። በቀብር ሥነ ሥርዐቶቻችን ላይ ትኩረታችን የሟቹን ሕይወት ማክበርና ማስታወስ ቢሆንም፣ በዋነኛነት ግን ሥነ ሥርዐቱን ለታደሙት ሊሆን ይገባል።

ስብከተ ወንጌል በግልጽ የሚነገርበት ነው። ምናልባት ስለ ሞተው ሰው መዳን በግላችን መተማመኑ ካለን፣ ስለሚቀበለው ሰማያዊ ሽልማት መናገር መልካም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የማናውቀው ሰው ከሆነ አልያም ስለ መዳኑ ርግጠኛ ካልሆንን፣ ለአድማጮቻችን መሠረት የሌለው የውሸት ማጽናኛ ከመናገር መቆጠብ አለብን፤ ይልቅ ትኵረት ለእነርሱ ሰጥቶ ወንጌልን መናገር አስፈላጊ ነው።    

የቀብር ሥነ ሥርዐት ስብከት ከ20 ደቂቃ ሳይበልጥ፣ ከታች የምናያቸውን ሦስት ምድቦች በማጉላትና ከመጽሐፍ ቅዱስ በማብራራት መቅረብ አለበት።

1. የማዘን አስፈላጊነትን ዕውቅና መስጠት         

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ከሞት ያስነሣው የአልዓዛር ታሪክ በቀጥታ ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው። ኢየሱስ ወዳጁን በማጣቱ ካለቀሰ፣ የእኛም ማልቀስ ተገቢ ነው። አንድ ጊዜ ሁለተኛ ልጃችን ሲጨነግፍብን፣ አባቴ እኔንና ባለቤቴን አስቀምጦ ያስተማረንን ሁልጊዜ  እናገረዋለሁ፤ ለሐዘኑ ጊዜ መውሰድ እንዳለብንና ይህንንም እንዴት እንደምናደርግ አስተምሮናል።

ሰዎች ማዘናቸው ተገቢ እንደ ሆነ፣ ወይም ስለ ሟች ዘመዳቸው በማውራት ከሐዘናቸው እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ያውቃሉ ብለን ማሰብ የለብንም። በርግጥ ብዙ ሰዎች ሐዘናቸውን ማጋራት፣ ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ ሐዘን ቀስቃሽ ነገር እንደ ሆነ ያስባሉ። ብዙ መጋቢያን እንደሚያውቁት ግን ከዓመታት በኋላ ሰዎች የዚህን ሂደት ጥቅም መረዳት ይጀምራሉ።

2. የወንጌልን ተስፋ በግልጽ ማሳወቅ                      

በሐዘን ውስጥ ያለ ሰው፣ እውነተኛውን ተስፋ በወንጌል ካለው ተስፋ ውጪ ከየትም አያገኝም። ሁለተኛውና ሦስተኛው የስብከት ክፍል በክርስቶስ ማንነትና ሥራ ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው። ሰለዚህ ለመስበክ የተመረጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከየትኛውም ቢሆን፣ ግልጽ በሆኑ የወንጌል ይዘቶችና ክፍሎች ላይ መናገር መቻላችሁን ርግጠኛ ሁኑ። ይኸውም፣ የእግዚአብሔርን ቅድስና፣ የሰውን ኀጢአተኝነትና ፍርድ የሚገባው መሆኑን፣ እንዲሁም የኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ መምጣትና የማስተሰረይ ሥራ ሊነገር ይገባል። ይህን የማዳን ሥራ በማመንና ንሰሓ በመግባት ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ማድረግ ተገቢ ነው።

3. ለተሰበከው ወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ አድማጮችን መጋበዝ

ስለ አድማጮቻችን ማወቅ፣ ይህን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ይረዳናል። የቀብር ሥነ ሥርዐቱን በታደሙት መካከል ክርስቲያኖችም ብሎም ክርስትያን ያልሆኑ ሰዎች እንዳሉ መገመት አለብን። ግምቱ ውስጥ መግባት የሚኖርበት ሌላው ነገር፣ የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ያላቸው ግንዛቤ  ነው። ለምሳሌ፣ ዘጠና በመቶ ያህሉ ካቶሊኮች በሆኑበት ዐውድ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በብዛት ሞርሞኖች በተገኙበት ቀብር ላይ፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ሰዎች መካከል የቀብር ሥነ ሥርዐት አድርጌ ዐውቃለሁ።

ለሁሉም እንደየሁኔታቸው ወንጌልን በግልጽ ካስረዳሁ በኋላ፣ በክርስቶስ እንዲያምኑና እርሱን እንዲታመኑ፣ በመጨረሻም ንሰሓ እንዲገቡ ጥሪ አቀርባለሁ። በእያንዳንዱ አጋጣሚዎች ግን፣ ስለ ወንጌል ባላቸው መረዳት ላይ ተመሥርቼ ለወንጌሉ በተለያየ መልኩ ምላሽ እንዲሰጡ አደርጋለሁ። እንዲያዝኑ ማበረታታት፤ ወንጌልን በግልጽና በቀላሉ መናገር፤ ሞት ከፊታቸው ስለ ሆነ ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ለማስረዳት መሞከር፤ ከዚያም እንዲያምኑና ንስሓ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረብ በቀብር ቦታ ላይ ወንጌልን በአግባብ ለመስበክ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በብራየን ክሮፍት