የክሕደት ረቡዕ ጠዋት
ረቡዕ በጸጥታ የተዋጠ ሆኖ ዐለፈ። በታላቅም ዝምታ የተሞላ ነበር።
ያለፉት ሦስት ቀናት በድራማ ተጥለቅልቀው ነበር። ይኸውም የእሑዱ የድል አድራጊነት ጕዞ፣ የሰኞው የቤተ መቅደሱ መንጻት፣ እና የማክሰኞው የቤተ መቅደሱ ውዝግቦች ናቸው። አሁን ግን ሚያዝያ 1 ቀን በ33 ዓ.ም. የዋለው ረቡዕ ከማዕበሉ በፊት እንዳለ ጸጥታ ሆኖ መጣ።
ነገር ግን ከእይታ ውጭ፣ በጨለማ ውስጥ አድፍጦ፣ ክፋት ሊንቀሳቀስ እየተዘጋጀ ነበር። በኢየሱስ ላይ የነበረው የጨለማ ሴራ ከውጪ ባሉ ጠላቶች ብቻ ሳይሆን አሁን ከውስጥ ባለው ከዳተኛም ጭምር ወደ ፊት ስለ ተንቀሳቀሰ፣ ቤተ ክርስቲያን ይህን ቀን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ፣ “የክሕደት ረቡዕ (Spy Wednesday)” ስትለው ኖራለች። በታሪክ ውስጥ ለተፈጸመው ታላቅ ኀጢአት ሴራ፣ ይኸውም የእግዚአብሔርን ልጅ ለመግደል ቊልፍ አካላት አንድ ላይ የተሰባሰቡት በዚህ ቀን ነበር።
ሴራው እየጠነከረ መጣ
ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባረፈበት በቢታንያ በማርያም፣ ማርታና አልዓዛር ቤት ዐደረ። ትምህርቱም ብዙ ሕዝብን እንደ ገና ወደ በቤተ መቅደሱ ሰበሰበ። በትላንትናው ዕለት ኢየሱስ ዝም ያሰኛቸው የአይሁድ መሪዎች አሁን ግን ትተውታል። ዛሬ በአደባባይ መጋጨትን በማስወገድ በምትኩ በድብቅ ሴራን ይሸርባሉ።
ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ የካህናት አለቆችንና ፈሪሳውያንን በግል መኖሪያ ቤቱ ሰበሰበ። በተለምዶ የሚቃረኑት እነዚህ ሁለት ቡድኖች የገሊላውን ሰው ለማጥፋት ባላቸው የጋራ ፍላጎት አሁን በአንድነት ይሠራሉ። ሊገድሉት አሲረዋል፤ ነገር ግን ገና ሁሉንም ነገር አላሟሉም። እርሱን የሚደግፈውን ሕዝብ ፈሩ። በፋሲካ በዓል ወቅት የተሰበሰበውን ሕዝብ ለማነሣሣት አልፈለጉም። የመጀመሪያው ዕቅድ፣ ያልታሰበ አጋጣሚ ካልተፈጠረ በቀር ከበዓሉ በኋላ እስኪሆን መጠበቅ ነበር።
በዚህ ጊዜ ከዳተኛው ብቅ አለ።
ስስታሙና ገንዘቡ
ሁሉም የወንጌል ዘገባዎች መነሻ የሆነውን ቀጣዩን ታሪክ ይናገራሉ፤ ይኸውም በቢታንያ የተደረገው የኢየሱስ ሽቱ መቀባት ነው።
አንዲት ሴት ወደ ኢየሱስ ቀረበች፤ በዮሐንስ ወንጌል 12፥3 ላይ እንደምንማረው እርስዋ የማርታ እኅት ማርያም ነበረች። እርስዋ “ዋጋው እጅግ የከበረ ሽቱ” ወስዳ ኢየሱስን ቀባችው። ከደቀ መዛሙርቱ ተቃውሞ መጣ፤ ዮሐንስ 12፥4 ይህን ያለው ይሁዳ መሆኑን ይናገራል። “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” አለ። ይህ ከወታደር ወይም ተራ ሠራተኛ የዓመት ደመወዝ የሚበልጥ “እጅግ ብዙ ገንዘብ” ነበር። አንድን ቤተ ሰብ ከአንድ ዓመት በላይ ለማስተዳደር የሚበቃ ገንዘብ ነበር፤ እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ብዙ ሊያገለግል ይችል ነበር።
ነገር ግን ኢየሱስ የይሁዳን ስስታምነት አልተጋራም። እዚህ ላይ ይህን አባካኝነት በትክክለኛው ቦታው ላይ አገኘው። እርሱ የሚያመጣው መንግሥት ተግባራዊ የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ብቻ ትኲረትን ማድረግ ያወግዛል። በማርያም “ብክነት” ውስጥ ከምክንያታዊ፣ ከተሰላ የጊዜና የገንዘብ አጠቃቀም ዐልፎ የሚሄድ የአምልኮ ፍላጎትን ይመለከታል። ለማርያም፣ ኢየሱስ ካላት ገንዘብ በላይ የላቀ ዋጋ አለው። ይህ የመቀባት ድርጊቷ ራሱ፣ ያደረገችው ነገር “መልካም ሥራ” እንደ ሆነ ይናገራል (ማቴዎስ 26፥10)።
ይሁዳ ግን፣ ይህ ጕዳይ አላሳመነውም። ከሚመስለው በተቃራኒ፣ የስስታሙ ሰው ተቃውሞ የስግብግብነትን ልብ ያሳያል። የይሁዳ ጭንቀት የመጣው፣ “የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቍሮ አልነበረም” (ዮሐንስ 12፥6)። ከዳተኛው ለረጅም ጊዜ በኀጢአትና በልብ መደንደን አቅጣጫ ውስጥ ቈይቷል፤ ነገር ግን የመጨረሻው ገፊ ምክንያት፣ ይህ እጅግ ውድ ቅባት ነበር።
በዚህ ገንዘብ በሚወድድ ልብ ውስጥ ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳን አገኘ፤ ይህን ተከትሎም የባሰ ክፋት መጣ። የዓመት ደመወዝ በሆነው በዚህ “ብክነት” ተቈጥቶ፣ ወደ ካህናት አለቆች በመሄድ፣ ሴረኞቹ ይፈልጉት የነበረውን አጋጣሚ ፈጠረ። ሰላዩ ሕዝቡ በተበተነበት አመቺ ጊዜ ወደ ኢየሱስ ይመራቸዋል። ይህ ስግብግብ ሰው፣ በዘፀአት 21፥32 መሠረት የአንድ ባሪያ ሕይወት ዋጋ በሆነው ሠላሳ ብር ብቻ ይህን ያደርጋል።
መከዳት ለምን?
እግዚአብሔር ለምን እንዲህ እንዲሆን ፈቀደ? ኢየሱስ በርግጥ በ”እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ” (ሐዋርያት ሥራ 2፥23) ተላልፎ ከተሰጠ፣ ደግሞም፣ ጠላቶቹ የእግዚአብሔር እጅና ዕቅድ “ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም” (ሐዋርያት ሥራ 4፥28) እያደረጉ ከሆነ፣ ከገዛ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ እንዲሰጠው ዕቅዱን የነደፈው ለምንድን ነው? የመስቀሉ መከራ ሳያንስ ለምን ክሕደት ተጨመረ?
ኢየሱስ የይሁዳን መክዳት ሲተነብይ መዝሙር 41፥9ን በመጥቀሱ አንድ ፍንጭ እናገኛለን፡- “እንጀራዬን የበላ፣ የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣ ተረከዙን አነሣብኝ” (ዮሐንስ 13፥18)። ንጉሥ ዳዊት በጠላቶቹ የተሴረበትን ብቻ ሳይሆን፣ በጓደኛም የመከዳትን ሥቃይ ያውቅ ነበር። ስለዚህ አሁን የዳዊት ልጅ በሥቃዩ ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ ይጓዛል። እዚህ ጋር ይሁዳ በርሱ ላይ ጠላት ሆኖ ተነሣበት። በቅርቡ ጴጥሮስ ይክደዋል፣ ከዚያም የቀሩት ዐሥሩ ይበተናሉ።
ከአደባባይ አገልግሎቱ መጀመሪያ አንሥቶ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከጐኑ ነበሩ። ከርሱ ተምረዋል፤ ከርሱ ጋራ ተጕዘዋል፤ ከርሱ ጋራ አገልግለዋል፤ የምድር ጓደኞቹ ነበሩ፤ እናም ብቸኛ በሆነው ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ ሲጓዝ አጽናንተውታል።
አሁን ግን፣ የኢየሱስ ሰዓት ሲደርስ፣ ይህን ሸክም ብቻውን መሸከም ነበረበት። ይህ አስፈላጊው የመጨረሻ ሥራ የቡድን ጥረት አይሆንም። ወዳጆቹ እንኳ ሲክዱትና ሲበተኑ፣ የተቀባው ብቻውን ወደ ፊት መጓዝ አለበት። ዶናልድ ማክላውድ እንዳስተዋሉት፣ “የዓለም መቤዠት በደቀ መዛሙርቱ ትጋት (ወይም ከእንቅልፍ ነቅተው በመጠበቃቸው) ላይ እንኳ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ፣ ፈጽሞ ባልተከናወነ ነበር።”
በአትክልቱ ስፍራ፣ “ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋራ” (ዕብራውያን 5፥7) ጸሎቱን ሲያቀርብ፣ በነበረው የሐዘን ስሜት ላይ ዳዊት የገጠመው የልብ ስብራት ተጨምሮበታል፦ “እንጀራዬን የበላ፣ የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣ ተረከዙን አነሣብኝ” (መዝሙር 41፥9)። በቅርብ የምድር ወዳጆቹ የተተወ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ እርሱን የሚሰልለው ሆኗል። ነገር ግን ከባዱ ሥቃይ ይህ ብቻ አልነበረም። ከባዱ ሥቃይ የመጣው፣ “አምላኬ አምላኬ፣ ስለ ምን ተውኸኝ?” በሚለው የመተው ጩኸት ውስጥ ነው (ማቴዎስ 27፥46)።
ሆኖም ከዚህ የመተው ጥልቀት በላይ እርሱ የሚያሳየው የፍቅር ጥግ እጅግ አስገራሚ ነው። እነርሱ ቢተዉትም፣ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።