መለወጥ፣ እግዚአብሔር እና ሁለንተናዊ ማንነት

ሰዎች እንዲድኑ እና እግዚአብሔርን እንዲያውቁ መለወጥ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍት ግልጽ ያደርጋሉ። ከኀጢአታችን ዞር ብለን ወደ እግዚአብሔር ካልተመለስን፣ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ የልብ መገረዝ ብሎ የሚገልጸውን እውነት በተግባር እስካላወቅን ድረስ እግዚአብሔርን በማዳኑ አናውቀውም(ዘዳግም 30፥6ሮሜ 2፥25-29)። ደግሞም ከፍርዱና ከቁጣው በታች እንሆናለን (ኤፌሶን 2፥1-3)።

ቶም ሽራይነር በ9ማርክስ ጆርናል በጻፈው ሁለት አምዶቹ እንዳሳየው፣ መላው መጽሐፍ ቅዱስ የመለወጥን አስፈላጊነት ያስተምራል። መለወጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ዋና ሐተታ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በርግጥ ለጠቅላላው የመቤዠት ታሪክ መሠረት ነው። በተለይም መቤዠት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ባለው ተዛምዶ ከመለወጥ ጋር ይያያዛል። ከመለወጥ ውጪ እግዚአብሔርን በማዳኑ መንገድ ማወቅ አንችልም። የኀጢአትን ይቅርታ ማግኘት አንችልም። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እና የማዳኑ አገዛዝም መግባት አንችልም።

ነገር ግን፣ አሁንም፣ መለወጥ ለምን አስፈለገ? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል።

ስለ መለወጥ ሰፊ ተቀባይነት ባለው ግንዛቤ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው ግንዛቤ መካከል ንጽጽር

ጥያቄውን ከመመለሳችን በፊት፣ ስለ “መለወጥ” እየተነጋገርን ያለነው የቃሉን የተዛባ ትርጉም ይዘን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ መሠረት መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው። ልዩነቱ ምንድን ነው?

በ “መንፈሳዊ ለውጥ” ላይ የጎግል ፍለጋን ካደረግን፣ ዋናዎቹ መልሶች ይህን ይመስላሉ፦ መለወጥ፣ “አዲስ ሃይማኖት መቀበል ነው” ወይም “አዲስን እምነት መከታተል” ነው። እነዚህ ትርጓሜዎች “መለወጥ” የአንድ ሰው አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ለውጥ አድርገው ብቻ ይመለከቱታል። ይህም በአብዛኛው ጊዜ ግለሰቡን በቀድሞ ሕይወቱ እንዲቀጥል ያደርገዋል። ነገር ግን ይህ የክርስትና መለወጥ አይደለም።

ክርስቲያናዊው ለውጥ/መለወጥ/ አሀዱ ሥሉስ የሆነው አምላክ በሰዎች ሕይወት ውስጥ በሚሠራው ሉዓላዊ እና ልዕለ ተፈጥሮአዊ ሥራ ላይ የሚደገፍ ነው። በመለወጥ፣ እግዚአብሔር ሰዎችን ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ሕይወት ያመጣቸዋል። ይህም በአንድ ወቅት ይወዱት የነበረውን ማለትም ኀጢአታቸውን እና በእግዚአብሔር ላይ ማመፃቸውን እንዲጸየፉ፣ ደግሞም ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱና እንዲታመኑት ያስችላቸዋል።

የመለወጥን አስፈላጊነት የሚያስረግጡ ሦስት እውነቶች

ይህ የመለወጥ ግንዛቤ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ሦስት መሠረታዊ እውነቶች ስለ መለወጥ መጽሐፍ ቅዱስ  የሚያስተምረውን ትምህርት ደግፈው ይይዛሉ። እነዚህም እውነቶች መለወጥ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በነገረ መለኮት እና በወንጌል አዋጅ ውስጥ ለምን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንድናይ ይረዱናል።

እነዚህ ሦስት እውነቶች ሙሉ በሙሉ እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን አጽንኦት ልስጥ። እነዚህን ሌሎች እውነቶች ካልተረዳን በቀር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚያስተምረውን በትክክል ልንረዳው አንችልም። ይህም በቀላሉ ነገረ መለኮታዊ እምነቶቻችን እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን ያስታውሱናል። በአንድ ነገረ መለኮታዊ ጉዳይ ስሕተት ውስጥ መግባት በሌሎች ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። ይህም በእርግጠኝነት ስለ መለወጥ ባለን ግንዛቤም ተመሳሳይ ውጤት አለው።

የሰው ችግር

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚያስተምረውን ግልጽ የሚያደርግልን የመጀመሪያው መሠረታዊ እውነት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ችግር ያለው ምልከታ ነው። ምንም እንኳ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክ በክብር ብንፈጠርም፣ በአዳም በኩል በፈጣሪያችን ላይ በማመፅ ከእግዚአብሔር ቁጣ በታች ያሉ ኀጢአተኞች ሆነናል (ዘፍጥረት 3ሮሜ 5፥12-21)።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኀጢአት እና ስለ ሰው ልጆች ኀጢአተኝነት ሲናገር ይህን እንደ ትንሽ ችግር አይመለከተውም። የተሻለ ሰው ለመሆን በራስ ጥረት፣ በተጨማሪ ትምህርት ወይም በግል ውሳኔ እንኳ የሚስተካከል ነገር አይደለም። እንዲህ ያሉ በየወቅቱ የሚቀርቡ መፍትሔዎች ቅዱሳት መጻሕፍት በብርቱ እና በግልጽ የሚያብራሩትን የሰውን ልጅ ችግር ምንነት በእጅጉ ያቃልላሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ፣ ኀጢአት የቃል ኪዳን ወኪላችን በሆነው በአዳም ምክንያት ለሁሉም ሰው የተረፈ የዓለም ጦስ ብቻ አይደለም (ሮሜ 3፥9-12235፥12-211ኛ ቆሮንቶስ 15፥22)። በተጨማሪም ይህ እውነት በተፈጥሮ እና በድርጊት ኀጢአተኞች እንድንሆን ያደርገናል (ኤፌሶን 2፥1-3)። በአዳም እና በራሳችን ምርጫዎች በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ወደዚህ ዓለምም የወደቁ ፍጥረታት ሆነን መጥተናል። ይህ ሁኔታ በራሳችን ተነሣሽነት እና ተግባር መለወጥ የማንችለው ነው። በሚያሳዝን መልኩ ደግሞ፣ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጸጋ ውጭ ይህ ሁኔታችን እንዲለወጥም አንፈልግም። በውድቀታችን፣ በኀጢአታችን መደሰት እና በእኛ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ትክክለኛ አገዛዝ በፈቃደኝነት መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ራሳችንን ለማዳን እና ለመለወጥ እንደማንችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው (ሮሜ 8፥7)። በውጤቱም ዕውቅና ሰጠነውም አልሰጠነውም፣ በእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ሥር እንቆማለን (ሮሜ 8፥1 ኤፌሶን 2፥1-3)። በኀጢአታችን ውስጥ ሆነን፣ በአጽናፈ ዓለሙ ዳኛ ፊት ያለንበት ሁኔታ በኩነኔ እና በጥፋተኝነት ነው (ሕዝቅኤል 18፥20ሮሜ 5፥1215-198፥1)። ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን ሁኔታ እንደ ሞት ይገልጹታል፤ መንፈሳዊ በመጨረሻም ደግሞ ሥጋዊ ሞት ነው (ዘፍጥረት 2፥16-17ኤፌሶን 2፥1ሮሜ 6፥23)።

ለዚህ ችግር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መፍትሔ የሆነው ደኅንነት፣ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ይለውጠዋል። በዚህ ክስተት ውስጥ ዋናው ነጥብ መለወጥ የሚለው ሐሳብ ነው።

በመጀመሪያ የሚያስፈልገን ለኀጢአታችን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሚከፍል፣ በተጨማሪም የእግዚአብሔርን የጽድቅ መስፈርቶችና በእኛ ላይ ያለውን ፍርድ የሚያረካ አዳኝ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ለእኛ ሲል በመስቀል ሥራው ይህንኑ አደረገ። የእግዚአብሔርን የፍትሕ መስፈርቶች አሟላ፤ ኀጢአታችን ሙሉ በሙሉ ተከፍለ (ሮሜ 3፥21-26ገላትያ 3፥13-14ቈላስያስ 2፥13-15ዕብራውያን 2፥5-18)።

በተጨማሪም፣ የኀጢአታችን ዕዳ መከፈል ብቻ ሳይሆን፣ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ሕይወት ልንመጣ ያስፈልገናል። ይህም በማንነታችን ላይ ሙሉ በሙሉ ለውጥን ያስከትላል (ሮሜ 6፥1-23ኤፌሶን 1፥18-232፥4-10)። እግዚአብሔር ከሞት ወደ ሕይወት ሊጠራን እና በእግዚአብሔር መንፈስ በኩል አዲስ ልደት ሊሰጠን ያስፈልገናል (ኤፌሶን 1፥3-14 ዮሐንስ 3፥1-8)። ከኀጢአታችን እንድንመለስ፣ በእግዚአብሔርና በአገዛዙ ላይ ያለንን ተቃውሞ አስወግደን ለወንጌሉ በንስሓና በእምነት ምላሽ እንድንሰጥ ከኪዳናችን ራስ ትንሣኤ ጋር የሚመሳሰል ትንሣኤ ያስፈልገናል (ዮሐንስ 3፥56፥441ኛ ቆሮንቶስ 2፥14)።

በጥቅሉ፣ መለወጥ አስፈላጊ የሆነው በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተገለጸው ለሰው ልጅ ችግር አሳሳቢነት የመፍትሔው አካል ስለሆነ ነው።

አስተምሮተ እግዚአብሔር

ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የመለወጥ አስፈላጊነት ትምህርት የሚያጸናው እና ትርጉም እንዲሰጥ የሚያደርገው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና እና ባሕርይ የሚያስተምረው እውነት ነው።

ከላይ እንደ ተገለጸው፣ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ አንዳቸው ሌላቸውን ግልጽ ያደርጋሉ። የሰው ችግር ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የተገናኘ ነው። ችግራችን በእውነተኛ ቀለሞቹ ሊታይ የሚችለው ከእግዚአብሔር ጻድቅ እና ቅዱስ ባሕርይ አንጻር ብቻ ነው።

መለወጥ አስፈላጊ የሆነው ኀጢአተኛ እና ዐመፀኛ ፍጥረታት ሆነን በእግዚአብሔር ቅዱስ መገኘት ውስጥ መኖር ስለማንችል ነው። ኀጢአት የአጽናፈ ዓለሙ ገዢ የሆነው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማራከስ ብቻ ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ኪዳናዊ መገኘትም ለይቶናል (ዘፍጥረት 3፥21-24ኤፌሶን 2፥11-18ዕብራውያን 9)። እግዚአብሔርን እንድናውቅና ወኪል አስተዳዳሪዎች በመሆን እንደ ታናናሽ ልዑላን እና ለዕልት ለእግዚአብሔር ክብር በፍጥረት ላይ እየገዛን እንድንኖር የተበጀነው እኛ፣ አሁን በእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ሥር ቆመናል።

ስለዚህ፣ እግዚአብሔር በልጁ ባደረገው የመሥዋዕት መግቦት የእርሱ ቅዱስ ባሕርይ ካልረካ በቀር፣ በማዳኑ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም (ሮሜ 6ኤፌሶን 4፥20-24ቈላስያስ 3፥1-14)። በተጨማሪም፣ በእግዚአብሔር ፊት በመጽደቃችን የፍርድ መሻር አስፈላጊ ቢሆንም፣ በቂ ግን አይደለም። ድኅነት ኀጢአትን ከውስጣችን ማስወገድን እና የወደቀውን ተፈጥሮአችን መለወጥን ያካትታል። ይህ የሚጀምረው በመንፈስ ሥራ ዳግም በመወለድ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስንሆን ነው። ይህም በፈቃደኝነት ከኀጢአት ተመልሰን በጌታችን በክርስቶስ የተጠናቀቀ ሥራ እንድናርፍ ያስችለናል።

በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ስለሚፈልግ መለወጥ የግድ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በፊቱ እንድንኖር የክርስቶስን ጽድቅ ልንለብስ፣ በመንፈስ ኀይል ተለውጠን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት ልንሆን ይገባናል (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥17-21)። የኀጢአታቸው ዕዳ ሙሉ በሙሉ ሳይከፈል፣ በመንፈስ ዳግመኛ ሳይወለዱ፣ ከክርስቶስ ጋር በእምነት አንድ ሳይሆኑ፣ ሰዎች ወደ ተፈጠሩበት ዓላማ የሚመለሱበትና በአዲስ ፍጥረት የሚገኘውን ጥቅም ሁሉ የሚያገኙበት መንገድ የለም።

ቅዱሱና ፍጹም ጻድቁ እግዚአብሔር፣ ፍጥረታቱ እንደ ታዛዥ ልጆችና በአምሳሉ እንደ ተበጁ ፍጡራን ይመላለሱ ዘንድ እንደሚፈልግ መረዳት ካልቻልን፣ መለወጥ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ፈጽሞ አይገባንም።

በተጨማሪም፣ የእኛ መለወጥ የሚከናወነው በአሀዱ ሥሉሱ አምላክ ሉዓላዊ ጸጋ ብቻ እንደሆነ ካልተረዳን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ለሕዝቡ ያለውን የፍቅሩን ጥልቀት እና ስፋት ሙሉ በሙሉ አናደንቅም።

መለወጥ ንስሓን እና እምነትን ያካትታል፦ የሁለንተናችን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚሰጠውን ትምህርት እንድንረዳ የሚረዳን ሦስተኛው መሠረታዊ እውነት፣ መለወጥ ሁለንተናን የሚያካትት ለውጥ መሆኑ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት፣ መለወጥ ሁለቱንም ማለትም ከኀጢአት መመለስን (ንስሓ) እና ወደ ክርስቶስ መዞርን (እምነት) ያካትታል። ሁለቱም ለመለወጥ አስፈላጊ ናቸው። በተጨማሪም ንስሓ እና እምነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።

በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መለወጥ በግለሰቡ ሕይወት ላይ ምንም ለውጥ የማያመጣ የዕውቀትና የአመለካከት ለውጥ ብቻ ሊሆን በጭራሽ አይችልም። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በብዙ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ተለውጠናል የሚሉ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ የለውጥ ማስረጃ ሳይኖር፣ ስለ ወንጌል ያላቸውን አእምሮአዊ ዕውቀት ብቻ ይገልጻሉ።

ቅዱሳት መጻሕፍት ይህን ዐይነት የዕውቀት ብቻ የሆነ ለውጥ እንደ ሐሰተኛ ለውጥ ይመለከቱታል (ማቴዎስ 7፥21-23)። እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ ፍጥረታት ለእርሱ ሁለንተናዊ ምላሽ እንድንሰጥ ይጠይቀናል። ኀጢአታችን በእግዚአብሔር ላይ የተደረገ ሁለንተናዊ ዐመፅ ነው። የክርስቲያን መዳን ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ ነው። በቀላል አገላለጽ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። መለወጥ ከኀጢአት መመለስን እና ወደ ክርስቶስ መዞርን ያካትታል፤ ይህም ሁለንተናን ማለትም ሐሳብን፣ ፈቃድን እና ስሜትን ያካትታል (የሐዋርያት ሥራ 2፥37-382ኛ ቆሮንቶስ 7፥10ዕብራውያን 6፥1)።

ኢየሱስ ባርኔጣችንን ማውለቅ ብቻ በቂ አይደለም

መለወጥ አማራጭ አይደለም፤ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ደኅንትን እና ወንጌልን ስለ መለወጥ ካለን ጠንካራ ዕይታ ውጭ ልንረዳው አንችልም።

በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የተንሰራፋው ‘የስም ክርስትና’ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና አይደለም። ባርኔጣችንን ማውለቅ ብቻ በቂ አይደለም። ይልቁኑ ንስሓ ለመግባትና ወንጌልን እንድናምን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ አዲስ ሕይወት በማግኘት በሕይወታችን ውስጥ ሉዓላዊ ጸጋ ከተሞላበት የእግዚአብሔር አሠራር ጋር ልንገናኝ ይገባል።

ስለ መለወጥ ያለን የተሳሳተ ግንዛቤ ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ ነገረ መለኮቶቻችን ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው። ለዚህ መፍትሔው በመንበርከክ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት መመለስ ነው፤ ደግሞም ታላቁ አምላካችን ቤተ ክርስቲያኑን እንደገና እንዲያነቃቃና በወንጌል አዋጅ ሰዎች ሁሉ ከኀጢአታቸው ንስሓ እንዲገቡና በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያምኑ መጠየቅ ነው።

በስቴፈን ጄ. ዌለም