ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ አንድ እምነት አለኝ። ይህም፣ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት አዲስ እና ዘላቂ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን ነው። ይህ ጽኑ እምነት፣ ቢያንስ ለእኔ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድ እና እንዲያነቃቃን ወይም እንዲያበረታን ያለው የቤተ ክርስቲያን ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ እምነት የኢየሱስ ክርስቶስን አገዛዝ ለሌሎችም ሆነ ለእኛ እንዲገልጥልን ካለን ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። ልክ እንደ እኔ፣ ይህ አስተሳስብ በልባችሁ እና በአምሮአችሁ ውስጥ በአዲስ ጉልበት እና ኀይል እየሞላ ከሆነ፣ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥሩ ሊሆን ይችላል፦ “ይህ አስተሳስብ በውስጣችን መስረጹን እንዴት እናውቃለን?” ማለትም “በርግጥ እንደተቀበልነው፣ እንዳመንበት የሚያረጋግጠው ነገር ምንድን ነው?”
የጸሎት ትጋት
በቅርቡ፣ በእነዚህ ዐይነት ጥያቄዎች ላይ እያሰላሰልኩ ነበር፤ እናም ቢያንስ ሁለት ምልክቶች የሚታዩ ይመስለኛል። በመጀመሪያ፣ ይህ እምነት የጸሎት ትጋት በሚኖርበት ጊዜ ራሱን ይገልጻል። የሚጸልየው ሰው “ያገኘዋል።” በእውነቱ ከሆነ፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ፊት የሚሄዱት ብቻ እምነቱን በእውነት ይጎናጸፋሉ ብዬ አስባለሁ። በጸሎታቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የመታደስ ሥራን ማከናወን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ማመናቸውን ያሳያሉ። እኛ የማንጸልይ ሰዎች ከሆንን ሥራውን በራሳችን እንደምናሳካ ማሰባችንን ያመለክታል።
ትክክል ከሆንኩ፣ ማለትም ጸሎት የእኛ ጽኑ እምነት ግልጽ ማስረጃ ከሆነ፤ እግዚአብሔር በዘመናችን አዲስ የወንጌል ሥራ እንዲሠራ የሚመኙ ሰዎች የሚጸልዩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው።
የሚገርመው፣ በሉቃስ ወንጌል ዋና ነጥቦች ውስጥ፣ ይህ ዐይነቱ ቁርኝነት ተገልጿል። ቢያንስ አራት ጊዜ ሰዎች ኢየሱስን ማን እንደ ሆነ ሲለዩት ከሚጸልይ ሰው ጋር አያይዞት ነበር።
-ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ከመቀበሉ በፊት ኢየሱስ ብቻውን ሲጸልይ ነበር (9፥18-20)።
- ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጡ። ከዚያም ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹም ከዚህ ዕውቀት አንጻር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመግለጥ ከሰማይ የእግዚአብሔር ድምጽ መጣ (9፥28-36)።
- ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት፣ ሰማያት ሲከፈቱ፣ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ፣ እና ከሰማይ የመጣ ድምፅ ኢየሱስን ልጁ መሆኑን ሲያረጋግጥ እየሱስ እየጸለየ ነበር (3፥21-22)።
- አረጋውያኑ ቅዱሳን ስምዖን እና ሐና ኢየሱስን በማንነቱ ያወቁት በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እና በመደበኛው የጸሎት ጊዜ ነበር።
እነዚህ አራት ሁነቶች አስፈላጊ ናቸው። እንደ ንድፍ ተሰጥተውናል ብዬ አምናለሁ። ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ እና እርሱን መከተል ሲጀምሩ በአዲስ እና ቀጣይነት ባለው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፣ ይህንንም በጸሎት በኩል እንደሚያደርጉት ያስተምሩናል።
መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስፈልገን ከልብ ከተቀበልን ፣ ራሳችንን ለጸሎት እንሰጣለን።
ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ገለጭ ስብከት መገዛት
ሁለተኛ፣ ለአዲስ እና ለዘላቂ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እምነት እና መሻት ሲኖረን ጸሎት ብቻ አይደለም መታወቂያው። ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ገላጭ ስብከት ያለን ቁርጠኝነትም አብሮ ብቅ ይላል። ቤተ ክርስቲያን ለታላቁ መሻታችን መልስ እየሰጠች ስትሄድ ሰዎችም ሆኑ ሰባኪዎች ለእግዚአብሔር ቃል መገለጥ እየተራቡ ይመጣሉ። በሌላ መንገድ፣ በጸሎት እየተጋ ያለው ያ ሰው ራሱ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው ገላጭ ስብከትም ራሱን በውዴታ ይሰጣል።
መንፈስ ቅዱስ እና ስብከት አብረው የሚሠሩ ናቸው
ብዙ አንባቢዎች፣ በመንፈስ ቅዱስ እና ስብከት መካከል ያለውን ግንኙነት አልተረዱም። ደግሞም ብዙዎቻችን ለመንፈስ ቅዱስ ወይም ለእግዚአብሔር ቃል ከመሰጠት አንዱን መምረጥ እንዳለብን በስሕተት ተነግሮናል። አንድ ሰው “የአስተምህሮ ሰው” ወይም “መንፈሳዊ ሰው” መሆንን መፈለግ ይችላል፤ ነገር ግን ሁለቱንም በአንዴ መሆን አይችልም ይባላል።
እንዲህ የሚሉት ሰዎች “በመንፈስ የሚመራ ቤተ ክርስቲያን” ወይም “ቃሉን ማዕከል ያደረገች ቤተ ክርስቲያን” መካከል አንዱን መምረጥን እንዲያምን ይፈልጋሉ። ነገር ግን አንድ ሰው በአንዴ በሁለቱም መገኘት አይችልም ይላሉ። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ እኛ መካከል ሥር ሰድዷል። ነገር ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።
እውነቱን ለመናገር፣ ለዚህ ዐይነቱ ክርክር ዝያለሁ። መንፈስ እና ቃል እርስ በርሳቸው የተጋጩ አስመስለው ውይይቱን በዚህ መንገድ ከሚያካሄዱት ጋር መነጋጋር አድካሚ ሥራ ነው። ይህ ዐይነቱ መነጣጠል ውሸት ነው። እናም ይህን ችግር እንዴት ማለፍ እንዳለብን የምንማርበት ጊዜ ነው።
በዚህ ምትክ የእኔ ክርክር፣ የመንፈስ ቅዱስን አዲስ እና ዘላቂ ሥራ በቤተ ክርስቲያን እንዲሆን የሚፈልግ ሰው ለጸሎት ብቻ ሳይሆን ለቃለ እግዚአብሔርም ራሱን የሰጠ ሰው ነው የሚል ይሆናል። ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ምንጊዜም ሰንሰለታዊ በሆነ መልኩ ከቃሉ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው።
ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ ምሳሌ መውሰድ
ምንም እንኳ ብዙ ሊመረጥ ይችል የነበረ ቢሆንም ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ጽሑፍ በቂ ነው። ዕብራውያን 3፣ በተለይም ቁጥር 7ን ተመልከት፣ በዚህ መንገድ ነው የሚጀምረው፦ “ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል….” በእነዚህ አራት ቃላት ውስጥ ሁለት አስደናቂ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፣ ይህን አስተውል! ጸሐፊው መዝሙር 95ን ሲጠቅስ የመንፈስ ቅዱስን ደራሲነት በማመልከት ነው። እርሱ “መጽሐፍ እንደሚለው” ወይም “መዝሙረኛው እንዳለው” ወይም “ጽሑፉ እንዳለው” አላለም። ይልቁንስ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” ሲል ጽፏል።
ይህ ትልቅ ቁም ነገር ነው። የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ ለመስማት ከፈለጋችሁ፣ ይህ ድምፅ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጋር ይዛመዳል። ይህም ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የገለጸው ቃል እንዳለ ያሳያል። እንዲህ ብሎ በትዊተር የለጠፈው ጆን ፓይፐር ይመስለኛል፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ሲያናግርህ መስማት የምትፈልግ ከሆነ ክፍልህ ውስጥ ግባ፣ በሩን ዝጋ፣ እና መጽሐፍ ቅዱስን ጮክ ብለህ አንብብ።” እኔም እስማማለሁ። የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ነው። ስለዚህ፣ የእኛ እምነት እና ፍላጎት የቤተ ክርስቲያን አዲስ እና ዘላቂ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከት ላይ እኩል ቁርጠኝነት ማድረግ ያስፈልገናል።
በዕብራውያን 3፥7 ላይ ያለው ሁለተኛው አስገራሚው ነገር የጥቅሱ የሰዋሰው መደብ ግሥ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው! እንዲህ ይነበባል፦ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል…” የዚህም ጠቀሜታ ሊታለፍ አይገባም። መዝሙር 95፣ ቀድሞ በተለየ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ጥንታውያን ሕዝቦች የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል፣ ሕያው ቃል ሆኖ ለኋለኛው ትውልድም እንዲሁ ነው ተብሏል። ዛሬም ቢሆን ለእኛ እንዲሁ ነው። ዕብራውያን 3፥7 በአሁን ጊዜ ባለው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እና በተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል መካከል ቀጣይ እና ሰንሰለታዊ ግንኙነት ይመሠርታል።
ማጠቃለያ
ለተሃድሶሃዊው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጽኑ እምነት ያስፈልጋል። እናም የጸሎት እና የቃለ እግዚአብሔር ስብከት በሚገኙበት ጊዜ ይህ ጽኑ እምነት በአጥንታችን ዘልቆ እንደ ገባ እናውቃለን። በቅርብ ቀናት ውስጥ፣ ይህ ጽኑ እምነት በአዲስ ኀይል እና ጉልበት ወደ ነፍሴ ውስጥ እየገባ ነበር። ይህ እምነት ትክክለኛ መሆኑን ተረዳሁ ምክንያቱም ጸሎት እና ስብከት ከጊዜ ወደ ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ውጤት እያመጡ ስላየሁ ነው። ለአንተም/ ለአንቺም እንዲሁ እንዲሆን እመኛለሁ።
በዴቪድ ሄልም