“የክርስቶስ እጮኛ አመንዝራ ልትሆን አትችልም፤ ያልተበላሸች እና ንጽሕት ናት። አንድ ቤት ታውቃለች፤ በንጽሕና ቅድስናዋን ትጠብቃለች። ለእግዚአብሔር ትጠብቀናለች። የወለደቻቸውን ለመንግሥቱ ትሾማለች። ማንኛውም ከቤተ ክርስቲያን ተለይቶ ከሴተኛ አዳሪ ጋር የሚተባበር፣ ከቤተ ክርስቲያን የተስፋ ቃል ተለይቷል። የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን የተወ፣ የክርስቶስን ሽልማት ማግኘት አይችልም። እርሱ እንግዳ ነው፤ ጸያፍ ነው፤ ጠላትም ነው። ቤተ ክርስቲያን እናቱ እስካልሆነች፣ እግዚአብሔር አባቱ ሊባል አይችልም።
— ሳይፕሪያን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ 6.
የሃይላንድ ቪሌጅ የመጀመሪያው ባፕቲስት ቸርች (አሁን ቪሌጅ ቸርች እየተባለ የሚታወቀው) ፓስተር ስሆን 28 ዓመቴ ነበር። ቀደም ብሎ በቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ ነገር አጋጥሞኝ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አባልነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን በወቅቱ እርግጠኛ አልነበርኩም። ይህም ሆኖ፣ በዳላስ ከተማ ዳርቻ ያለችውን ይህችን ትንሽ ቤተ ክርስቲያን እረኛ እንደምሆን መንፈስ ግልጽ አድርጎልኝ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት በሕይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ብዙ አስቂኝ ነገሮች አንዱ ይህ ነበር።
የሃይላንድ መንደር የመጀመሪያው ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ “Seeker Sensitive” ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ እናም ምንም ዐይነት መደበኛ የአባልነት ሂደት አልነበራትም፣ ምንም እንኳ በአንድ ላይ በንቃት እየሠሩ እና የአዲሱን ፓስተር ግብዓት ቢፈልጉም። ስለ ዩኒቨርሳል ቤተ ክርስቲያን ጠንከር ያለ ግንዛቤ ነበረኝ ፤ነገር ግን ስለዚያች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብዙም አላውቅም ነበር። ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሌላቸው፣ ወይም መጥፎ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደግ ካላቸው ወጣቶች ጋር በፍጥነት ማደግ ጀመርን። እኛ “የተለያየን” ስለነበርን መንደሩን ወደውታል። ከመስበክ እና ከመዘመር በቀር ምንም እያደረግን ስላልነበር ይህ ሁልጊዜ እንግዳ ነገር ሆኖብኛል።
ከእነዚህ ወንዶችና ሴቶች ጋር ባደረግኩት ውይይት “ቤተ ክርስቲያን ተበላሽታለች” የሚሉ ነገሮች መስማት ጀመርኩ። ስለ ገንዘብ እና የፓስተር “እኔ ልታይ ባይነት” ብቻ ነው፣ ወይም “ኢየሱስን እወዳለሁ! ችግር ያለብኝ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። በጣም የወደድኩት ደግሞ ‘ቤተ ክርስቲያንን ስትደራጅ ኀይሏን ታጣለች’ የሚል ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ በእነዚህ አስተያየቶች በውስጤ አንዳንድ ነገር ያስተጋባል (እኔ ከአብዛኛው የእኔ ትውልድ ጋር የሥልጣን እና የቁርጠኝነት ጉዳዮች አሉኝ) እኔ ፓስተር በነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ በነበሩ ሰዎች እየነገሩኝ ስለነበር ግራ የሚያጋቡኝ ሆኖ አግኝቻቸዋለሁ።
ሁለት ጥያቄዎች ከዕብራውያን 13፥17
ዋነኛ ብዬ የማስባቸው ሌሎች አስተምህሮዎች ግጭቶች እየተፈጠሩ ባሉበት ጊዜ፣ ይህ የቤተ ክርስቲያን አባልነት ነገር ወደ ጎን አድርገን ቆይተን እንመለሳለን ብዬ አሰብኩ።
በወቅቱ የዕብራውያንን መጽሐፍ ለመስበክ እየተዘጋጀሁ ነበር፤ እናም ቁጥር 17 ምዕራፍ 13 ላይ “ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጕዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው፤ አለዚያ አይበጃችሁም” ይላል።
ሁለት ጥያቄዎች መጡብኝ። በመጀመሪያ፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርት ከሌለ፣ ታዲያ አንድ ክርስቲያን ለየትኞቹ መሪዎች ነው መታዘዝ እና መገዛት ያለበት? ሁለተኛ፣ በግል እኔ እንደ ፓስተር ተጠያቂ የምሆነውስ ለማን ነው?
እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለኝን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ ፍለጋዬን የጀመሩ ሲሆን የጀመሩት በሥልጣን እና በመገዛት ሐሳቦች ዙሪያ ነበር።
የመጀመሪያውን ጥያቄ በተመለከተ ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲገዙና እንዲያከብሩ በግልጽ ያዝዛሉ (ዕብራውያን 13፥17፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥17)።
የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል ካልሆንን፣ ለማን እንታዘዝ? ለየትኛውም ቤተ ክርስቲያን “ሽማግሌ” የሚሆን ሰው አለ? እንደ ክርስቲያን አጉል የሆነ ልምምድ እና ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላለው “ቤተ ክርስቲያን” ሸማግሌ ወይም መጋቢ የመታዘዝ ግዴታስ አለበት?
ሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ ሽማግሌ የተወሰኑ ሰዎችን እንዲንከባከብ በግልጽ ያዝዛሉ (1ኛ ጴጥሮስ 5፥1-5፣ እንዲሁም የሐዋርያት ሥራ 20፥29-30)። እኔ እንደ አንድ መጋቢ፣ በምኖርበት ትልቅ ከተማ ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ተጠያቂ እሆናለሁ? በምኖርበት ከተማ ውስጥ ጠንካራ የነገረ መለኮት እና የፍልስፍና ልዩነት ያላቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ የሚያስተምሩትን ወጣቶች፣ በየ አብያተ ክርስቲያኑ ያሉ አባላት ያላቸውን ገንዘብ አጠቃቀም፣ ቅድስናቸውን፣ የወንጌል ስብከት ልምዳቸው ላይ ሁሉ ተጠያቂ እሆን ይሆን?
ስለ ቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊንስ ምን ማለት ይቻላል?
የሥልጣን ጥያቄዎችን ከተመለከትኩ በኋላ፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጥናቴ ላይ የመጣው ሁለተኛው ጉዳይ ስለ ቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው።
ይህን ትምህርት በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እናያለን፤ ነገር ግን ከሁሉም ግልጹ 1ኛ ቆሮንቶስ 5፥1-12 ይመስለኛል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በግልፅና ንስሓ በሌለው የዝሙት ርኩሰት የሚመላለስ ሰውን ስለመቀበሏ ይከሳታል። የቆሮንቶስ ሰዎች ይህን እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ይዘውታል፤ ነገር ግን ጳውሎስ እንደዚህ ዐይነት ክፋት እንዲመኩበት ሳይሆን እንዲያዝኑበት አስጠንቅቋቸዋል።
ትዕቢተኞች ብሎ ይጠራቸውና ይህን ሰው ሥጋው ጠፍቶ ነፍሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ ከመካከላቸው እንዲያስወግዱት ለእነርሱም ይነግራቸዋል። በቁጥር 11-12 ላይ፦ “ነገር ግን አሁን የጻፍሁላችሁ፣ “ወንድም ነኝ” እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋር እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋር ምግብ እንኳ አትብሉ። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔን ምን አግብቶኝ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን?”
በጣም ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት አሁንም የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊንን መተግበራቸው አሳዛኝ ገጠመኜ ነው፤ ግን ያ ለሌላ ቀን ሌላ ጽሑፍ ነው። ከዚህ ጽሑፍ ውስጥ የእኔ ጥያቄ ቀላል ነው። አንድን ሰው ቤተ ክርስቲያን “ውስጥ” ከሌለ እንዴት ማስወጣት ይችላሉ? ለቃል ኪዳን እምነት የአጥቢያ አባልነት ቁርጠኝነት ከሌለ፣ ታዲያ አንድን ሰው ከዚያ የእምነት ማኅበረሰብ እንዴት ያስወግዳሉ? የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ከሌለ የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን አይሠራም።
ለአባልነት ሌሎች ብዙ ማስረጃዎች
የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባልነትን ሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች አሉ።
በሐዋርያት ሥራ 2፥37-47 ስንመለከት በቁጥር በዚያ ያሉ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ ይላል (ቁ41) እናም ቤተክርስቲያኗ እድገቷን ትመዘግብ እንደነበር እናያለን (ቁ. 47)። በሐዋሪያት ሥራ 6፥1-6 የተፈጠሩ ግጭቶችን እና መካሰሶችን ለመፍታት ምርጫ ሲካሄድ እናያለን።
በሮሜ 16፥1-16 የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል እነማን እንደነበሩ ግንዛቤ እንደነበራቸው እናያለን።
በ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥3-16 በግልጽ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ባልቴቶች እንዴት ማገልገል እንዳለብን እናያለን። ከቁ 9-13 እንዲህ ይላል፦ “ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት ያነሰ መበለት በመዝገብ ላይ አትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት። ወጣት መበለቶችን ግን እንዲህ ባለው መዝገብ አትጻፋቸው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ በገቡት ቃል ላይ በሚያይልበት ጊዜ ለማግባት ይሻሉና። በዚህም ፍርድን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በመጀመሪያ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። በተጨማሪም ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጕዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።”
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ማን በኤፌሶን ላሉ መበለት እንክብካቤ ለማድረግ ብቁ እንደሚሆን ወይም እንደማይሆን መመዘኛዎችን እንመለከታለን። የኤፌሶን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተደራጀች እና በዕቅድ የምትመራ ነበረች።
በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 ወይም ሮሜ 12 ላይ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የቃል ኪዳን ማኅበረሰብ ጋር ካልተገናኘን ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት እንዴት መታዘዝ እንችላለን? ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ ሁሉንም ነገር ማውራት ብዙ ጊዜ ያስፈልገዋል።
የእግዚአብሔር ዕቅድ እኛ የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል እንድንሆን ነው
እነዚህን ክፍሎች መመልከት ስንጀምር፣ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ያለው ዕቅድ እኛ የአጥቢያ የቃል ኪዳን የእምነት አባል መሆናችንን እንደሆነ ግልጽ ይሆንልናል። ይህ ለራሳችን ጥበቃ እና ብስለት፣ ደግሞም ለሌሎች ጥቅም ነው።
ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ ዐይነት ሥነ ምህዳራዊ ቡፌ የምትመለከቱ ከሆነ፣ የማደግ ዕድላችሁን በእጅጉ ይገድባሉ። እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ማደግ ሊጎዳ ይችላል። ለምሳሌ፣ በገዛ አጥቢያዬ ውስጥ ከሌሎች ጋር ስገናኝ፣ የራሴ ቅናት፣ ትዕግሥት ማጣት፣ ደካማው የጸሎት ሕይወቴ፣ እና ድሆችን መርዳት አለመፈለጌ ግልጥልጥ ብሎ ይወጣል(ሮሜ 12፥11-16)።
ሆኖም ይህ መስተጋብር ከእኔ ጋር አብረውኝ ካሉ ወንድሞች እና እኅቶች ጋር በፍቅር እንድጋፈጥ እድል ይሰጠኛል፣ እንዲሁም መናዘዝ እና ንስሓ ለመግባት አስተማማኝ ቦታ ይሆነኛል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ሳትቀላቀሉ ባላችሁበት ስትሆኑ፣ ልክ እንደ ቤተ ክርስቲያን ቡፌ፣ ልባችሁ በመንፈስ መጋለጥ በጀመረ ቁጥር ሁል ጊዜ ወደ ፊት ትሄዳለህ፤ እና ትክክለኛውም ሥራ ይጀምራል።
ታዲያ ምን እያልኩ ነው? የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል የመሆን ያለመሆን ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስን የመታዘዝ እና ያለመታዘዝ ጥያቄ እንጂ የግል ምርጫ አይደለም።
በማት ቻንድለር