ሰባኪዎች ለማን ነው የሚሰብኩት? በቅርብ ብዙ ስለ ስብከት የተጻፉ መጻሕፍትን ከመደርደሪያዬ ላይ አውርጄ እያገላበጥኩ ነበር፤ እናም የተገለጠለኝ ነገር ቀድሜ የጠየቅኩትን ጥያቄ ብዙም ሲመለከቱት አላየሁም። ሰባኪዎች አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጡት ስብከታቸውን ማረም ላይ ነው።
አሁንም ቢሆን ጥቂት መጋቢያን ናቸው ለታዳሚዎቻቸው (ለሰሚዎቻቸው) ትኩረት የሚሰጡት። ብዙ ጊዜ ትኩረታቸው የሚያጋድለው ሁለት የማኅበረሰቡ ክፍሎች ላይ ነው፤ ማለትም ቤተ ክርስቲያን አልባዎችንና ድህረ ዘመናውያኖችን። የጎርደን ኮንዌል ፕሬዝዳንት ጄምስ ኢመሪ ዋይት በቻርሎት፣ ሰሜን ካሮላይና የመክልንበርግ ማኅበረሰብ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር፣ በአንድ ወቅት ከላይ የተነሡት ክፍሎች በዋነኝነት የማያምኑት ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል። እ.ኤ.አ. በ1999 በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ እንዲህ አስቀምጠውታል፦
መክልበርግ እውነትን ፈላጊዎች ላይ አተኮሮ የሚሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ማለትም እውነትን ፈላጊ ቤተ ክርስቲያን አልባ ሰዎች ላይ ያተኩራል። ይህን ስንል፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚስቡ ነገሮች ለእነዚህ እውነትን ፈላጊ ቤተ ክርስቲያን አልባ ሰዎች ታስበው ነው የተዘጋጁት። በየትኛውም ዐይነት ፤ መንገድ ወይም ቅርጽ እነዚህ ሰዎች እውነትን ሲፈልጉ ስናገኛቸው መርዳት የምንፈልገው ቀጣይነት ባለው መንገድ እውነትን እንዲፈልጉ ማድረግ ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን አልባ የሆነ ሰው ሁሉ እውነትን ፈላጊ ስላልሆነ።
ስብከት ደግሞ ወደ ሕይወታቸው የመግቢያ አንዱ መንገድ ስለሆነ፣ ዋይት ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን አልባ የሆኑ ሰዎችን በስብከታቸው ለመድረስ የለዩት የእነ ቢል ሄብልስ፣ ቦብ ራስል እና ሪክ ዋረን አርአያ ተከታይ ናቸው።
ሌሎቹ ጎራዎች ደግሞ በድህረ ዘመናዊ አስተሳሰብ ለተያዙ ሰዎች የመስበክን አስፈላጊነት ይጽፋሉ። የቀድሞው መጋቢ ብራያን ማክላረን የድህረ ዘመናዊነት ተውኔታዊነትና ዝርዝር ትንታኔ ጠልነት፣ እንዲሁም ራስን መሆንና ትረካ አፍቃሪነት ስብከታቸውን እንደ ቀረጸው በ2001 ስለ ድህረ ዘመናዊነት ባላቸው ምልከታ ላይ ተናግረው ነበር። አሁን ላይ ትረካና ራስን መሆን የስብከታቸው ማዕከል ነው።
እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው ሁለት ምሳሌዎች ለአንዳንዶቻችን ሊያስፈሩን ይችላሉ። በሲከር ሴንሴቲቭና (seeker-sensitive) በኢመርጀንት ቤተ ክርስቲያናት (Emergent churches) እንደምናየው ሰባኪ አድማጮቹን ለመድረስ በጣም ሩቅ በሄደ መጠን መልእክቱ ሊቀየጥ ይችላል። አሁንም ግን ሰባኪዎች ወደድንም ጠላንም ለእውነተኛ ሰዎች ማለትም ለቤተ ክርስቲያን አልባ ሰዎች፣ ለድህረ ዘመናውያን እንዲሁም ለብዙ ዐይነት ሰዎች ነው የሚሰብኩት። ስለዚህም ፈታኙ ነገር በጉባኤ ውስጥ ላሉ ለተለያዩ ዐይነት ሰዎች ሐሳቦችን ማቀበል ነው። ይሄ ጽሑፍም በትሕትና ለማድረግ የሚሞክረው ይህንኑ ነው።
መጋቢዎች ሦስት ዐይነት ሰዎችን ታሳቢ አድርገው ቢሰብኩ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።
ላልዳኑት ስበክ
ቤተ ክርስቲያናችን በቁጥር ጥቂትና ያልዳኑ ሰዎች ሁሌም የማይገኙበት ቢሆንም እንኳ ሁሌም ያልዳኑ ሰዎችን እሳቤ ውስጥ ያስገባ የእሁድ መርኅ ግብር ቢኖረን ጥሩ ነው። እኔ ያለሁበት ቤተ ክርስቲያን በቁጥር ትንሽ ነን፤ ሆኖም ግን ሁሌም ከተቀመጡት ሰዎች መካከል ክርስቶስን የማያውቁ እንዳሉ አስባለሁ። አንዳንዶች የአፍ ክርስቲያን ናቸው፤ ክርስቲያን ነን ብለው አምነው ለብዙ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ቢመጡም እውነቱ አዲስ ሕይወት እንዲኖራቸው ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ አባላት የጋበዟቸው አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ ለብዙ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን የራቁ ናቸው። በሌላ አነጋገር አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ይመጣሉ ማለቴ ነው።
ስለዚህ ምን እናድርግ?
ወንጌልን ግልጽ አድርግ
የሰባኪ ኀላፊነት ሁሌም የእግዚአብሔርን ቃል ሲገልጥ ወንጌልን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ ነው። ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፤ “’ኢየሱስ ጌታ ነው’ ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳሥነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና” (ሮሜ 10፥9-10)።
ሁላችንም የወንጌሉ አገልጋዮች ነን። ወንጌል ደግሞ በእያንዳንዱ ስብከት ውስጥ በአንድ ዐይነት መንገድ ግዴታ መነገር የለበትም። ሆኖም ግን መጋቢው ሁሌም ቢሆን እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል እንዲህ ብሎ መጠየቅ አለበት፦ “ይህ ክፍል እንዴት ነው ወደ ወንጌል የሚጠቁመኝ?” የማያምኑ ሰዎች እንኳ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ ስብከትንና ወንጌል እንደ መዝጊያ መጨረሻ ላይ የሚለጥፍ ስብከትን መለየት ይችላሉ።
ቤተ ክርስቲያናችን አቅራቢያ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት አለ፤ እናም ብዙ መጋቢ ለመሆን እየተማሩ ያሉ ሰዎች መጥተው ይህን ጥያቄ ይጠይቁኛል፦ “ወንጌል በሁሉም ስብከት ውስጥ ግዴታ መኖር አለበት?” መልሱ፦ “አዎን” ለዚህም በትንሹ ሁለት ምክንያቶችን እሰጣለሁ። አንደኛ፣ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁሉ ትርጉም የሚሰጠው ወንጌል ስለሆነ ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ ያልዳኑት ሰዎች፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ” የሚለው ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባቸው ስለሚያስፈልግ (በእምነታቸው ለማደግ ክርስቲያኖችም ወንጌልን ደጋግመው መስማት አለባቸው!) ያላመኑት ራሱ ደጋግመው ወንጌልን ሊሰሙ ቢችሉም እውነታው ግን ዛሬ እግዚአብሔር እኔ ወደምሰብክበት ጉባኤ አምጥቶአቸዋል፤ ስለዚህም ወንጌል እንዲሞግታቸው በድጋሚ ስለ ዓለም፣ ስለ ኀጢአትና ስለ ድነት ያላቸውን እሳቤ መፈተን አለበት።
እንደ መጋቢ ላደርጋቸው ከሚገቡ ዋነኛ ነገሮች መካከል አንዱ ወንጌልን ግልጽ ማድረግ ነው።
በገላጭ አሰባበክ ዘዴ ስበክ
የማያምኑ ሰዎች በጉባኤ መካከል ስላሉ ለእነርሱ የሚጠነቀቁ መጋቢያን ገላጭ ስብከትን በመስበክ ይበልጥ ሊያገለግሏቸው ይችላሉ። አማኞች ያልሆኑ ሰዎች የምናምነውን ለምን እንደምናምን ማወቅ ይፈልጋሉ። ሕይወታችንና ነገረ መለኮታችን የእግዚአብሔር ቃል ላይ ስለ ተመሠረተ ልክ ለአማኞች እንደምናደርገው አማኝ ያልሆኑትንም ሰዎች በታማኝነትና በግልጽነት ወደ ቃለ እግዚአብሔር ብንመራቸው ይበልጥ እናገለግላቸዋለን።
ብዙ በዚህ ዘመን ያሉ ጸሐፍያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንቅስቃሴ በዚህ በድህረ-ዘመናዊው አስተሳሰብ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያላቸውም ሆነ ቤተ ክርስቲያን አልባ ሰዎች በትረካዊ መልክ ለሚሰበክ ስብከት ጥሩ ምላሽ አላቸው ይላል። የመከራከሪያ ሐሳባቸውም ሰዎች ታሪክ መስማት ይፈልጋሉ ነው። ጥሩ! እኔ ራሴ ታሪክ እወዳለሁ። ገላጭ ስብከት የመጽሐፍ ቅዱስን የታሪክ መስመር መስጠት አለበት፤ በውጤቱም የእግዚአብሔርን ሥራ በሰው ልጆች ያደረገውን የታሪክ መስመር ማምጣት አለበት፤ ይህም አማኝ ላልሆኑ ሰዎች የራሳቸውን የታሪክ መስመር እንዲያገኙ ያደርግልናል። መጋቢያን የሚጠበቅባቸው በገላጭ ስብከታቸው ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መዳሰስ ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ሲያደርጉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን “የእግዚአብሔርን ትልቅ የማዳን ሥዕል” ለመስጠት በማሰብ መሆንም አለበት። ይህ ነው እንግዲህ እውነትን ፈላጊ ለሆነ ሰው የሚስማማ ስብከት!
ከላይ ያነሳሁት እንቅስቃሴ ሌላ የሚያነሣው ሐሳብ ድህረ ዘመናዊ አስተሳሰብ ትክክለኛና እውነተኝነት ላይ ትልቅ አትኩሮት ይሰጣል የሚል ነው። ጥሩ! እኔም እውነተኛ መሆንን እወዳለሁ። ይህ ምርጥ ገላጭ ስብከትን ለመስበክ ምክንያት ነው። የታሸገበት ካርቶኑን ሳይሆን ውስጡ ያለውን ነገር እንመልከት። ማለትም ኢየሱስ ምን አስተማረ? ኢሳይያስ ምን ተነበየ? ጳውሎስ ምንድን ነው የጻፈው? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አሁን በዚህ ዘመን ከምንኖር ሰዎች ጋር በምን ይገናኛል? ይሄን ነው በቤተ ክርስቲያናችን የሚመጡ ያላመኑ ሰዎች ማወቅ የሚፈልጉት፤ ያልተቀባባውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት። በስተመጨረሻ ከእውነቱ ጋር ተስማሙም አልተስማሙም፣ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ነገር ነው፤ እኛ ግን የምንሰብከው ሰዎችን አስደስቶ ለመሳብ አይደለም።
ያላመኑ ሰዎችን ድረሷቸው
ለማያምኑ ሰዎች መዳን የሚሆን ስብከትን ለመስበክ የተወሰኑ ነገሮች ማድረግ እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን ምዕራፍና ቁጥሮችን ለይቶ እንዲያውቁት መናገር ላላመኑ ሰዎች ጠቃሚ ነው። ይህ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስን ማውጫ እንዲጠቀሙበት ይረዳቸዋል። አማኝ ያልሆነ ሰው አጠገቡ ያለ ሰው ሁሉ የአብድዩን መጽሐፍን ፈጥኖ ሲያወጣ፣ እርሱ ግን ግራ ሲጋባ ምን ሊሰማው እንደሚችል አስቡት።
ሐሳብ ቀስቃሽ የሆኑ መግቢያዎችንም አማኝ ላልሆኑ ሰዎች ልናብራራ ያለውን ክፍል እንዲገባቸው እንደ ድልድይ መጠቀምም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያክል ባለፈው ፋሲካ ያካፈልኩት ፈሪሳውያን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ባለመጾማቸው የተገረሙበትን፣ በሉቃስ 5፥33-39 የሚገኘውን ክፍል ነው። ኢየሱስም በሰርግ ላይ ሚዜዎች ሙሽራው እስካለ ድረስ አይጾሙም ብሎ ነው የመለሰላቸው፤ ከዚያም ቀጥሎ አዲሱን ወይን ባረጀ የወይን ማስቀመጫ ቆዳ ስለ መጨመር ምሳሌ ነገራቸው። የስብከቴ ርዕስም “ክርስቲያኖች ደስተኛ ናቸውን? የሚል ነበር። የስብከቴ መግቢያ እውነተኛ፣ ዘላቂ፣ ሕይወት ለዋጭ የሆነው ደስታ የሚገኘው ከሞት ከተነሣው ሙሽራ ኢየሱስ ጋር ስንሆን ነው የሚለውን ለማስተላለፍ ጥሩ ዕድል ፈጠረልኝ። ድሮም ክርስቲያን የነበሩ በመግቢያው ተጠቅመው ይሆን? እንደ ተጠቀሙ አስባለሁ፤ እነዚያን ሦስትና አራት ደቂቃዎች ለምን በእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ እንደምንሰበሰብ ተጨማሪ ማብራሪያና ድጋፍ ለሚፈልጉ ያላመኑ ሰዎችን ለመድረስ እንደ ዕድል ተጠቀምኩበት።
እነዚህ “ትንንሽ” ልምምዶች የተጠራቀመ ውጤት በጉባኤዎቻችን ላይ ማምጣታቸው አይቀርም። አማኞች፣ መድረኩ ያላመኑ ሰዎችን ያማከለ ሆኖ ሲያገኙት ብዙ ጊዜ አማኝ ያልሆኑ ጓደኞቻቸውን መጋበዝ ይጀምራሉ። ወንጌል ተኮርነት እውነት ፈላጊ የሆኑ ሰዎችን ያስረሳናል ማለት የተሳሳተ ትርጓሜ ነው።
ለዳኑት ስበክ
ምንም እንኳ ላልዳኑት መስበክ አስፈላጊ ቢሆንም በጌታ ቀን (እሑድ) የሰባኪ የመጀመሪያ ሥራው እና ዐላማው አማኞችን መድረስ ነው። ሰባኪ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን መገንባት አለበት፤ ምዕመናን ደግሞ መስማትና በተዘጋጀ ልብ የቤተ ክርስቲያን ራስ ለሆነው ለክርስቶስ መገዛት አለባቸው። የመጀመሪያ አድማጮቻችን እነርሱ ናቸው። ስለዚህም በስብከቴ ዝግጅት በመጀመሪያ አዕምሮዬ ውስጥ ያሉት አማኞች ናቸው።
ስለዚህ ሰባኪ እንዴት አማኞችን መድረስ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ እንመልከት።
አማኞችን አርም ደግሞም ገሥጽ
ከዮሐንስ እንደምንረዳው ኀጢአት በዚህ ምድር በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሁሌም መኖሩ አይቀሬ ነው “ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም” (1ኛ ዮሐንስ 1፥10)። በዚህ ክፍል ውስጥ በትንሹ የምንረዳው ዮሐንስ አማኞች ኀጢአትን አሳንሰው የማየት ብሎም ቅድስናቸውን ከፍ አድርገው የማየት፣ እንዲሁም ክርስቶስን የመካድ ፈተና እንዳለባቸው ነው። ከዚህም ሲያልፍ ጳውሎስ ሲጽፍ፣ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” ብሏል። ስለዚህም አንድ እረኛ ለክርስቲያኖች ሲሰብክ በእግዚአብሔር ቃል እውነት መገሠጹና ማረሙ አይቀሬ ነው።
ማንም መጋቢ ክርስቲያኖችን ተስፋ በማስቆረጥ መታወቅ አይፈልግም። ሆኖም ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት አንዱ የሚጠይቀው ነገር መጋቢ እንደ ሁኔታው አስፈላጊነት ተግሣጽ መስጠቱ ነው። ለዚህም ነው የሰባኪነት ጥሪን በቀላሉ ማየት የሌለብን። ለዚህ ሥራ ታማኝ ከሆንን እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይህን ጥያቄ መጠየቅ አለብን፦ “ይህ ክፍል በምን መልኩ እየገሠጸን ወይም በምን መልኩ እንድንለወጥ እየጠየቀን ነው?” ጸሎት አልባ መሆናችንን እየገሠጸን ይሆን ወይስ ሐሜት ወይም ደግሞ ጣዖታችንን? መልሱ የሚገኘው መጋቢው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሕይወትን ከማስተዋል ወይም ደግሞ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠሩ የሕይወት ተዛምዶዎችን ከማስተዋል ነው። ያም ሆነ ይህ ያለ ተግሣጽና ያለ እርማት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከት ሊኖር አይችልም።
ክርስቲያኖችን ማጽናትና ማበርታት
ስብከት ተግሣጽና እርማት ብቻ ስላልሆነ እግዚአብሔር ይመስገን። ይህ ማለት በስብከት አማኞችን በእግዚአብሔር ቃል ማጽናትም ማበርታትም ይጠበቅብናል። አማኝ በሁለንተናው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ይደገፋል። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” (ማቴዎስ 4፥4፤ ዘዳግም 8፥3)። ክርስቲያን ወደ ስብከት ሲመጣ ከሕይወት ቃል ለመመገብ ነው።
በርግጥ አማኝ ከእሑድ ውጭ የእግዚአብሔርን ቃል በሳምንት ውስጥ ይመገባል፤ ነገር ግን በጌታ ቀን ስንሰበሰብ ያለው ስብከት ሕይወታችንን ለማቆየት ዋነኛውን ሚና ይጫወታል። ቲቶ 1፥1-3ን ካየነው ጳውሎስ እንዴት የዘላለም ሕይወት በስብከት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንደሚገለጥ ይነግረናል። ክርስቲያኖች በስብከት ነው የሚመገቡት እናም ሕይወታቸውን የሚያቆዩት። ሁሌም አንድን ክፍል መጠየቅ ያለብን ጥያቄ “በዚህ ክፍል እንዴት ነው አንድን ክርስቲያን ማበርታት ሕይወቱን መጠበቅና ማቆየት የምንችለው?”
በስብከት አገልግሎቴ ውስጥ ይበልጥ ከሚያበረቱኝ ነገሮች አንዱ፣ ቤተ ክርስቲያኔ ስለማስፈልጋቸው ሳይሆን ሕይወት ሰጪ የሆነውን በስብከት የሚገለጠውን ቃል እንደሚያስፈልጋቸው አውቀው ሲሰበሰቡ ነው! ይሄ ነው የተጣለብኝ ኀላፊነት፣ መንፈሳዊ ምግባቸውን ማዘጋጀትና ማቀበል። ምን ዐይነት ዕድል ነው እግዚአብሔር በቃሉ ሕይወትን ለማቆየት፣ ለመመገብ፣ ለመገንባትና ለማነጽ እኔን መጠቀሙ!
ክርስቲያኖችን ማበርታትና መቀደስ
የእግዚአብሔር ልጅ ለአባቱ ልጆች ሲጸልይ አብ እንዲቀድሳቸውና የበለጠ ክርስቶስን እንዲመስሉ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ የተለያየ መከራንና ስድብን በተቀበሉት ቃል ምክንያት እንደሚደርስባቸው ያውቃል (ዮሐንስ 17፥14) ነገር ግን ከዓለም እንዲያስወጣቸው አልጸለየላቸውም። ነገር ግን እንዲቀደሱ ነበር ጸሎቱ። ክርስቲያኖች እንዴት ነው ቅዱስ የሚሆኑት? ኢየሱስ “ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው።” ብሎ ጸልዮላቸዋል (ዮሐንስ 17፥17)። የእግዚአብሔር መልዕክት ልጆቹን ይቀድሳል። ክርስቲያኖች የሚቀደሱት ወንጌልን እና ቃለ እግዚአብሔርን በሙሉ በመቀበልና ከሕይወታቸው ጋር በማዛመድ ነው። ቅዱስ ቃል ቅዱስ ሕዝብን ይፈጥራል።
በእርግጥ መቀደስ በዋነኝነት የእግዚአብሔር ሥራ ነው። እሱ ነው በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚሰራው (ፊልጵስዩስ 2፥13 ፤ ዕብራዊያን 13፥20-21)። ይህ ብቻም ሳይሆን ለእርሱ ክብርና ሞገስን እንዲያመጡ የሚያስፈልጋቸውን እዲኖራቸው የሚያረጋግጠውም እሱ ነው። ይሄም የሚከናወነው ቅዱሳን የእውነትን ቃል ለመስማት በሚሰባሰቡበት ጊዜ ነው። ክርስቲያኖች ሲሰበሰቡ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” መነቃቃታቸው የማያስደንቀው ለዚያ ነው (ዕብራውያን 10፥24)።
ሰባኪዎች የኀጢአተኞች ሕይወት ውስጥ ገብቶ የክርስትናን ሕይወት እንዲኖሩ የማበርታት አስደናቂ ዕድልና ኀላፊነት አለባቸው። በመዝሙር 1 ላይ የተባረከ ሰው የተመሰለው በእግዚአብሔር ሕግ የሚደሰት በምንጭ ዳር እንደ ተተከለ ፍሬያማና ጠንካራ ዛፍ ነው። በመዝሙር 1 የተቀመጠልን ምስልን ለመረዳት ብዙም አስቸጋሪ አይደለም። ክርስቲያን ፍሬያማና ጠንካራ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሕግ ሐሴት ሲያደርግና ሲመገበው ነው። ስብከት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰላሰል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ምንም እንኳ ሰባኪ የተባረከ ሰውን መፍጠር ባይችልም (እግዚአብሔር ይመስገን! ይህ የእግዚአብሔርና የመንፈሱ ሥራ ስለሆነ!) ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ የመመገብ የከበረ ዕድል ተሰጥቶታል። ሰባኪ በታማኝነት የእግዚአብሔርን ቃል በመስጠትና ዛፉን ከሳምንት ሳምንት፣ ከወር ወር፣ ከዓመት ዓመት በማጠንከር ልክ እንደዚያ የምንጭ ውሃ መሆን ይችላል።
በወሩ መጨረሻ ገንዘብ አለመጉደሉን እንደሚያረጋግጥ አካውንታንት ወይም ደግሞ ድርጅቱ እየተሳካለት እንደሆነ እንደሚያረጋግጥ የድርጅት አስተዳዳሪ ባይሆንም፣ ማን ያውቃል ሰባኪ የሰዎችን ልብ እና ሕይወት ቀይሮ ቢሆንስ? የመጋቢ ፍሬው በዚህ ምድር ባለን ሕይወት ብቻ አይለካም። የመጋቢን ፍሬዎች ሰብስበን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጥ አይቻልም ሆኖም ግን ፍሬዎቹ ሁሌም ይኖራሉ። የተሰበከው የእግዚአብሔር ቃል በጸጋው ኀጢአተኛውን ይቀድሳል፤ ያበረታል ደግሞም ለጸጋው ሥራ ያዘጋጀዋል።
ክርስቲያኖችን ማበረታታትና ማሳደግ
የክርስቶስ ተከታዮች የቃሉ አረዳዳቸውና አተረጓጎማቸው ማደግ አለበት። የክርስቶስ ተከታዮች አብዛኛውን ጊዜ በሐዋሪያት ሥራ 17 ላይ እንደምናያቸው የተሰበከው ቃል እውነት መሆኑን እንደመረመሩት እንደ ቤሪያ ሰዎች አይደሉም፤ ብዙ ጊዜ ስብከትን እንዴት እንደሚሰሙና እንደሚያብላሉ ስናይ ግድ የለሽነት ይታይባቸዋል። ጠንካራ ገላጭ ስብከት የክርስቶስ ተከታዮችን አዕምሮአቸውን እንዲጠቀሙ፣ እንዲያስቡና እንዲመረምሩ ያበረታታቸዋል። ጄምስ ደብሊው አሌክሳንደር ጥልቀት የሌላቸውን ስብከቶች ሲተች እንዲህ ብሏል፦
ጥልቀት በሌላቸው ስብከቶች ውስጥ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች፣ አዲስና ልብ የሚነኩ ምሳሌዎችን፣ ትክክለኛ የሆኑ የመከራከሪያ ነጥቦች፣ ጠንካራ ተግሣጾችን፣ እንዲሁም የሰዎችን ልብ መንካት ሊኖር ይችላል። በራሳቸው እንደ መድረክ ንግግር ካየናቸው ምንም እንከን ላይወጣላቸው ይችላል፤ ሆኖም ግን ቃሉን ከመግለጥ አኳያ ምንም ናቸው። በእስትንፋሰ እግዚአብሔር ተመርተው የጻፉ የቃሉ ጸሐፍያን ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን አይመልሱም፤ በክፍሉ ላይ የተነሡ ሐሳቦች ላይ ዕውቀቱ ያላቸው ሰዎች የሚሉትን አያማክሩም፤ ከዓመት ዓመት አንድ ሐሳብ ይደጋግማሉ እንጂ ትክክለኛ የሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎምን ምዕመናቸውን በስብከታቸው ማስተማር አይችሉም።
ክርስቲያኖችን ለእድገት የሚያበረታቱ ስብከቶች የማይገቡና የተወሳሰቡ መሆን የለባቸውም (እንደዚህ ያሉ ስብከቶች ዓላማ የሌላቸውና ለቃሉ ዓላማም ታማኝ አይደሉም!)። ሆኖም ግን ክርስትያኖችን ለእድገት የሚያበረታቱ ስብከቶች ከቃሉ ጋር ጊዜን ባሳለፉና ከቃሉ ጋር በተዋሃዱ ሰባኪያን የሚሰበኩ ስብከቶች ናቸው። ለስብከቱ ጊዜ ሰጥቶ በደንብ የሚዘጋጅ መጋቢ የሚያጠናውን ክፍል “እንዴት ክርስቲያኖችን ለእድገት ያበረታታል?” ብሎ እንኳን መጠየቅ ላይኖርበት ይችላል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ስሪቱ ለእድገት ለማበረታታት ስለሆነ ስንሰብከው ዓላማውን መፈፀሙ አይቀሬ ነው (ኢሳይያስ 54፥10-11)። የሰባኪ የጥረቱን ውጤት ምዕመኑ በስብከቱ ሲጠቀምበት የድካሙን ፍሬ ያያል።
እኔ በማገለግልበት ቤተ ክርስቲያን አነስ ያለ ቁጥርም ላይ ሰበክንም ሙሉ መጽሐፍን ለተከታታይ ሳምንታት ሰበክን (በቅርቡ የኢዮብን መጽሐፍን እንደሰበክን ማለት ነው) ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ለመሆን እንጥራለን። ከብዙ ዓመታት በኋላ የኮሌጅ ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን እየመጡ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚሰበከው ስብከት በክርስትና ሕይወታቸው እንዲያድጉ እያበረታታቸው ስለሆነ ነው። በቅርቡ በእድሜ ገፋ ያሉ ባልና ሚስት ቤተ ክርስቲያናችንን እንደ ወደዱት እየነገሩን ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ከስብከት በኋላ ምሳ ሰዓት ላይ መንፈሳዊ ውይይቶች እንዲኖራቸው እየረዳቸው ስለሆነ ነው። ከውጭው ዓለም ጋር በግሩም ሁኔታ እንግባባለን ወይም ደግሞ ስብከቴ አስደሳች ነው ማለት አይደለም፤ ብዙ የምናድግበት ነገሮች አሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ መጽሐፍ ቅዱስን እየገለጥን ነው፤ ይህ ደግሞ አስደሳችና ሕይወት ለዋጭ ነው!
ክርስቲያኖች ለቃሉ ታማኝ የሆነ ስብከት ይፈልጋሉ፤ ማለትም የሚያርም፣ የሚያስተካክል፣ የሚያጸና፣ ለቅድስና የሚያበረታና የሚያጠነክር ደግሞም የሚያሳድግ ስብከት ይፈልጋሉ።
እስካሁን ለማያምኑና ለሚያምኑ መስበክን አውርተናል፤ እናም ይሄን ልጥፍ ለመጨረስ ጥሩ ቦታ ላይ ያለን ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ሰባኪዎች የቤተ ክርስቲያን አባሎችንም ታሳቢ ያደረገ ስብከት መስበክ አለባቸው።
ለቤተ ክርስቲያን አባሎች እንደ አንድ አካል በማሰብ ስበክ
በአብዛኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በእሁድ ስብሰባቸው ላይ ከሚመጡ ሴትና ወንዶች አብዛኞቹ ለዛ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለእርስ በእርስ ኅብረት የተሰጡ ወይም ቃል የገቡ ሰዎች ናቸው። ይሄ በስብከታችን ውስጥ ልናስበው የተገባ ነገር ነው? አዎን ይመስለኛል።
ጳውሎስ በቆላስያስ ያሉ ምዕመናንን፣ “አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት…” ብሎ ነው የሚገልጻቸው (ቆላስይስ 2፥19)። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ብቻ ሳይሆኑ በቆላስያስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሰደዱና እግዚአብሔር በሚሰጠው እድገት እያደጉ ያሉ አማኞች ናቸው። በቆላስይስ 3፥15-16 ጳውሎስ ቀጥሎ እንዲህ ይላል፦ “እንደ አንድ አካል ሆናችሁ የተጠራችሁበት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።” አስተውሉ ጳውሎስ እንደ አንድ አካል ነው የሚያያቸው፤ እናም ደግሞ በቃሉ ዙሪያ ኅብረት እንዲኖራቸው ያስታውሳቸዋል። ይህ ደግሞ የሚሆነው በአንድነት በሚሰበሰቡ ጊዜ ቃሉን ሲዘምሩ ብሎም ቃሉ ሲሰበክ ሲሰሙ ነው።
ጳውሎስ በዚህ ክፍል ክርስቲያኖችን እንደ ግለሰብ እያናገራቸው ሳይሆን የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባላት እንደሆኑ አስቦ ነው መልዕክት እያስተላለፈላቸው ያለው። መሰባሰባቸው አንድነትን ያመጣው አካባቢያቸው ቅርብ ስለሆና ስለሚተዋወቁ አይደለም፤ ነገር ግን ይህ የሆነበት ምክንያት አንድ ዐይነት መታነጽና ትምህርትን በሚካፈሉ ጊዜ የክርስቶስ ቃል በልባቸው መኖሪያውን ስላደረገ ነው። ያ ነው የአንድነታቸው ምክንያት።
አሁንም ቢሆን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህ እውነት ነው። የቤተ ክርስቲያን አባላት ወደ አንድነት የሚመጡበት አንዱ መንገድ በእግዚአብሔር ቃል ስብከት ነው። ጆን ካልቪን ስለ ሰባኪ አገልግሎት በሚናገርበት ቦታ ላይ ይህን ነጥብ ግልጽ አድርጎ አብራርቶታል። ሰባኪ ነው ለቤተ ክርስቲያን አካል አንድነትን የሚያመጣው። በኤፌሶን 4 ስለ አንድ ተስፋ፣ አንድ ጌታ ፤ አንድ እምነትና አንዲት ጥምቀት በሚያወራው ክፍል ላይ ጆን ካልቪን እንዲህ ብሎ ምልከታውን አስቀምጧል፦
ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ለማስተካከል የሚጠቀምባቸው የሰዎች አገልግሎት አማኞችን በአንድ አካል አንድ ለማድረግ ወሳኝ ማሰሪያ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር የሚሰራው እንደዚህ ነው። እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚገኝ ያሳይ ዘንድ ስጦታዎችን ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ለአገልጋዮቹ ይሰጣል ፤ የመንፈሱን ኀይል በመልቀቅ ደግሞ ትርጉም የለሽና ፍሬ አልባ እንዳይሆኑ ይጠብቃቸዋል። በዚህ መንገድ ቅዱሳን ይታደሳሉ፤ ብሎም ይታነጻሉ። በዚሁ መንገድም በሁሉ ነገር ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ እናድጋለን፤ እርስ በርሳችንም እንያያዛለን። በዚሁ መንገድ ደግሞ በክርስቶስ ወደሚሆን ኅብረት እንመጣለ፤ን ብሎም ደግሞ ስብከት እያፈራ እስከሆነ ደረስ የጌታን አገልጋይ እንቀበላለን ደግሞም አስተምህሮውን አንንቅም። ይህንን መልክ ያለውን የቤተ ክርስቲያን አካሄድ ሊያስወግድ የሚፈልግ ወይም እንደ ምንም ነገር የሚያንቋሽሽ ማንኛውም ሰው ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ እያሴረ ነው ማለት ነው።
ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ ትኩረታቸውን አባል ባልሆኑ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በሚመጡ ሰዎች ላይ አድርገው በቁጥር እያደጉ ነው። እኛ ለምንድነው ትልቁ ትኩረታችንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አባል ሆነው በአካል ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ የምናደርገው? የዚህ ምክንያቱ የአዲስ ኪዳን ድብዳቤዎችን ስናይ ትልቁ ትኩረታቸው እነዚህ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አካል የሆኑ ሰዎች ላይ ስለሆነ ነው። ክርስትና ከተለያየ የሕይወት ዳራዎች የመጡ ሰዎች የጋራ ወንጌልን የሚካፈሉበት አውድ ያለው የሕይወት ዘይቤ ነው ፤ ቤተ ክርስቲያን ማለትም ይሄው ነው። ጳውሎስ እንደ ጻፈው፣ “አንድ ብልት ቢሠቃይ፣ ብልቶች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር፣ ሌሎቹም ብልቶች አብረው ደስ ይላቸዋል።” (1 ቆሮንቶስ 12፥26)። ይህ ልብሳችንን ሰብሰብ አርገን አንዳችን የአንዳችን ሕይወት ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከት በተደጋጋሚ ክርስቲያኖችን መድረስ ያለበት እንደ ግለሰብ ሳይሆን፣ ነገር ግን ግለሰቦችን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ለኅብረት ኑሮ ቃል እንደገቡ ሰዎች አድርጎ ነው። ስንሰብከ እያንዳንዱን ክፍል፣ “ይህ ቃል እንዴት የአንድ አካል የእምነት ማኅበረሰብ (አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ) ለሆኑት ከሕይወታቸው ጋር ማዛመድ ይቻላል?” ብለን መጠየቅ አለብን። ለቤተ ክርስቲያን አባላት ለይቶ መስበክ ትንሽ ወጣ ያለ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ይህን ማድረጋችን ለማያምኑትና ቤተ ክርስቲያን እየመጡ በታማኝነት አባል መሆን ለማይፈልጉ ሰዎች ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ትርጉም ያለው ሳቢ ሥዕል ነው! መጋቢ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለተቀላቀሉት ክርስቲያኖች ያለውን አድናቆት እና በይበልጥ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኑን አባላትን በቀጥታ እነሱን ማዕከል አድርጎ በስብከት ሲደርሳቸው ለእግዚአብሔር ቃል ያለውን ፍቅር ያሳያል።
ማጠቃለያ
“ሰባኪ ለማን ይሰብካል” የሚለውን ጥያቄ ሳሰላስል፣ በካርሌተን አውስትራሊያ ያለው የሴንት ጁድ ቪካር ፒተር አደም ከጻፈው ጋር እስማማለሁ፦ “የእግዚአብሔር፣ የክርስቶስና የቃሉ አገልጋዮች ከሆንን የስብከት አገልግሎት ጥሪ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የማገልገል ጥሪ ነው።” እውነት ነው ቤተ ክርስቲያን ለሌላቸው አባል ላልሆኑ ሰዎች አስበን መስበክ አለብን። ነገር ግን ዋነኛ ትኩረታችን እነርሱ ብቻ ከሆኑ የወንጌል እውነት ሊጠፋ ወይም መልእክታችን በጣም ቀጥኖ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልተመጣጠነ ምግብ ማግኘቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን አባል ላልሆኑ ሰዎች መስበክ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን በዋናነት በክርስቲያኖች ላይ ማተኮር እና ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቃል የገቡትን አማኞች አዘውትሮ የመናገርን ጥቅም ማስታወስ አስፈላጊ ነው።
በአሮን ሜኒኮፍ