ወንጌልን በቀብር ሥነ ሥርዐት  ላይ መስበክ

“ወደ ገነት እየጠቆምክ አትስበካቸው፤ አልያም ወደ ሲኦል። ነገር ግን ለታዳሚዎቹ ወንጌሉን ብቻ ስበክ።” ይህ በማላውቀው ሰው የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ስለ መስበክ ያገኘሁት ጠቃሚ ምክር ነው። የቀብር ሥነ ሥርዐታችን ምንም ዐይነት ቢሆን፣ ይህ ለተግባራችን ወሳኝ መርሕ ነው። በቀብር ሥነ ሥርዐቶቻችን ላይ ትኩረታችን የሟቹን ሕይወት ማክበርና ማስታወስ ቢሆንም፣ በዋነኛነት ግን ሥነ ሥርዐቱ ለታደሙት ሊሆን ይገባል።

ስብከተ ወንጌል በግልጽ የሚነገርበት ነው። ምናልባት ስለ ሞተው ሰው መዳን በግላችን መተማመኑ ካለን፣ ስለሚቀበለው ሰማያዊ ሽልማት መናገር መልካም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የማናውቀው ሰው ከሆነ አልያም ስለ መዳኑ ርግጠኛ ካልሆንን፣ ለአድማጮቻችን መሠረት የሌለው የውሸት ማጽናኛ ከመናገር መቆጠብ አለብን፤ ይልቅ ትኵረት ለእነርሱ ሰጥቶ ወንጌልን መናገር አስፈላጊ ነው።    

የቀብር ሥነ ሥርዐት ስብከት ከ20 ደቂቃ ሳይበልጥ፣ ከታች የምናያቸውን ሦስት ምድቦች በማጉላት እና ከመጽሐፍ ቅዱስ በማብራራት መቅረብ አለበት።

1. የማዘን አስፈላጊነትን ዕውቅና መስጠት         

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ከሞት ያስነሣው የአልዓዛር ታሪክ በቀጥታ ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው። ኢየሱስ ወዳጁን በማጣቱ ካለቀሰ፣ የእኛም ማልቀስ ተገቢ ነው። አንድ ጊዜ ሁለተኛ ልጃችን ሲጨነግፍብን፣ አባቴ እኔንና ባለቤቴን አስቀምጦ ያስተማረንን ሁልጊዜ  እናገረዋለሁ፤ ለሐዘኑ ጊዜ መውሰድ እንዳለብን እና ይህንንም እንዴት እንደምናደርግ አስተምሮናል።

ሰዎች ማዘናቸው ተገቢ እንደ ሆነ፣ ወይም ስለ ሟች ዘመዳቸው በማውራት ከሐዘናቸው እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ያውቃሉ ብለን ማሰብ የለብንም። በርግጥ ብዙ ሰዎች ሐዘናቸውን ማጋራት፣ ቁስል ላይ እንጨት እንደ መስደድ ሐዘን ቀስቃሽ ነገር እንደ ሆነ ያስባሉ። ብዙ መጋቢያን እንደሚያውቁት ግን ከዓመታት በኋላ ሰዎች የዚህን ሂደት ጥቅም መረዳት ይጀምራሉ።

2. የወንጌልን ተስፋ በግልጽ ማሳወቅ                      

በሐዘን ውስጥ ያለ ሰው፣ እውነተኛውን ተስፋ በወንጌል ካለው ተስፋ ውጪ ከየትም አያገኝም። ሁለተኛው እና ሦስተኛው የስብከት ክፍል በክርስቶስ ማንነትና ሥራ ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው። ሰለዚህ ለመስበክ የተመረጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከየትኛውም ቢሆን፣ ግልጽ በሆኑ የወንጌል ይዘቶችና ክፍሎች ላይ መናገር መቻላችሁን ርግጠኛ ሁኑ። ይኸውም፣ የእግዚአብሔርን ቅድስና፣ የሰውን ኀጢአተኝነትና ፍርድ የሚገባው መሆኑን፣ እንዲሁም የኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ መምጣትና የማስተሰረይ ሥራ ሊነገር ይገባል። ይህንን የማዳን ሥራ በማመን እና ንሰሓ በመግባት ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ማድረግ ተገቢ ነው።

3. ለተሰበከው ወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ አድማጮችን መጋበዝ

ስለ አድማጮቻችን ማወቅ፣ ይህንን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ይረዳናል። የቀብር ሥነ ሥርዐቱን በታደሙት መካከል ክርስቲያኖችም ብሎም ክርስትያን ያልሆኑ ሰዎች እንዳሉ መገመት አለብን። ግምቱ ውስጥ መግባት የሚኖርበት ሌላው ነገር፣ የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ያላቸው ግንዛቤ  ነው። ለምሳሌ፣ ዘጠና በመቶ ያኽሉ ካቶሊኮች በሆኑበት ዐውድ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በብዛት ሞርሞኖች በተገኙበት ቀብር ላይ፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ሰዎች መካከል የቀብር ሥነ ሥርዐት አድርጌ አውቃለሁ።

ለሁሉም እንደየሁኔታቸው ወንጌልን በግልጽ ካስረዳሁ በኋላ፣ በክርስቶስ እንዲያምኑና እርሱን እንዲታመኑ፣ በመጨረሻም ንሰሓ እንዲገቡ ጥሪ አቀርባለሁ። በእያንዳንዱ አጋጣሚዎች ግን፣ ስለ ወንጌል ባላቸው መረዳት ላይ ተመሥርቼ ለወንጌሉ በተለያየ መልኩ ምላሽ እንዲሰጡ አደርጋለሁ። እንዲያዝኑ ማበረታታት፤ ወንጌልን በግልጽ እና በቀላሉ መናገር፤ ሞት ከፊታቸው ስለ ሆነ ክርስቶስ ምን ያኽል እንደሚያስፈልጋቸው ለማስረዳት መሞከር፤ ከዚያም እንዲያምኑ እና ንስሓ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረብ በቀብር ቦታ ላይ ወንጌልን በአግባብ ለመስበክ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በብራየን ክሮፍት