የሆሣዕና እሑድ ችግር

የሆሣዕና እሑድ ማታ

ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን የሕማማት ሳምንት ቀን የሆሣዕና እሑድ (Palm Sunday) በማለት ስታከብረው ኖራለች። ለዚህም ምክንያቱ፣ ሕዝቡ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በፊቱ የዘንባባ ቅርንጫፎችንና ልብሶቻቸውን ስላነጠፉ ነው።

የወንጌል ጸሓፊዎች እንደሚነግሩን ሕዝቡ ተሰብስቦ፣ በደስታ እየፈነጠዘ፣ ኢየሱስ በቀስታ ወደ ከተማዋ በሚጋልብበት መንገድ ላይ ተኮልኩሎ ነበር። እርሱ በአህያ ላይ ተቀምጦ አንድ ርምጃ ወደ ፊት ሲጓዝ፣ በፊቱ ልክ እንደ ምንጣፍ የሚሆን ነገር እየተዘጋጀ ነበር። በአቅራቢያው ከሚገኙ ዛፎች የተቈረጡ አረንጓዴ የዘንባባ ቅርንጫፎች፣ እንዲሁም ከሕዝቡ ጀርባ ላይ የወለቁ ወፍራምና ያረጁ ልብሶች፣ እስራኤል ለረጅም ጊዜ ስትጠብቀው ለነበረችው መሲሕ የፍቅርና የክብር መግለጫ (tapestry of endearment) ሆነው ነበር።

ነገር ግን እንደ ፈሪሳውያን አባባል፣ ይህ ትልቅ ችግር ነበር።

ሕዝቡ ያለው ምን ነበር

በርግጥ ችግሩ የነበረው የዘንባባው ቅርንጫፎች ሳይሆኑ ሰዎቹ ይናገሩት የነበረው ነገር ነበር።

ሉቃስ እንደሚነግረን፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ በደስታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ “በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” እያሉ ይጮኹ ነበር (ሉቃስ 19፥38)።

አንዳንድ ፈሪሳውያን ኢየሱስ ሕዝቡን ዝም እንዲያሰኝ ሞከሩ። ሰዎች ለሚናገሩት ነገር፣ በተለይም “ንጉሡ የተባረከ ነው” ለሚለው ንግግራቸው እንዲገሥጻቸው ጠየቁት።

እንደሚታየው ፈሪሳውያኑ ገብቷቸዋል። ይህ ዝም ብሎ የተለመደ ሐረግ አይደለም። ይህ የእስራኤል አዳኝ ሲመጣ የሚደረግ አቀባበል ነው።

ይህ ሐረግ በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር ድል ደስ በሚሰኘው በመዝሙር 118 ላይ ይገኛል። በዚህ መዝሙር ቊጥር 22 ላይ፣ የተናቀው ድንጋይ “የማዕዘን ራስ” ሆኗል (መዝሙር 118፥22)። ይህ በእግዚአብሔር የተከናወነ ድንቅ ሥራ ሲሆን የድነትንም ቀን ያበስራል (መዝሙር 118፥23–24)። ይህ ቀን፣ እስራኤል ፈጽሞ አይመጣም ብላ ያሰበችው ለረጅም ጊዜ የተጠበቀው የመዳን ቀን ነው። ነገር ግን ይመጣል፤ መጥቷልም። መዝሙር 118፥25ም ይህን ተስፋ እንዲህ ይገልጸዋል፦ “አቤቱ፥ እባክህ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ አሁን አቅና።”(ቀ.ኀ. ሥ.)

ይህ ድነትና ስኬት ዝም ብሎ የተለመደ ነገር አይደለም። ድነቱ የሚመጣው፣ ሕዝቡን ሊያድን በተላከው፣ የእግዚአብሔር መሲሕ በሆነው በአንድ ሰው በኩል ነው። ስለዚህም በመዝሙሩ ውስጥ ጩኸቱ ይቀጥላል፣ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” (መዝሙር 118፥26)።

ምንም ጥርጥር የለውም፣ መነሻውን ከመዝሙር 118 ያደረገው ይህ በኢየሩሳሌም የሚንጫጫ ሕዝብ፣ ኢየሱስ መሲሑ መሆኑን እያወጀ ነው። ይህን ዕብደት እንዲያስቆምም ፈሪሳውያን ለኢየሱስ የነገሩት፣ ከዚህ የተነሣ ነው። ምን እያሉ እንደ ሆነ ይሰማሃል? እኛን ለማዳን የመጣህ መሲሕ እንደሆንክ ዐስበዋል። ዝም እንዲሉ ንገራቸው።

ነገር ግን ኢየሱስ አላስቆማቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ ሕዝቡ ዝም ቢል፣ ድንጋዮች ራሳቸው እንደሚጮኹ ተናገረ። በርግጥም፣ ኢየሱስ መሲሕ ነው። እርሱ ሕዝቡን ሊያድን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል።

ሕዝቡ እንደሚለው ከሆነ ግን፣ ይህ ራሱ ችግር ነበር።

ሕዝቡ ያየው

ነገር ግን፣ ችግሩ የነበረው መዳኑ ላይ ሳይሆን ኢየሱስ መዳንን በሚያመጣበት መንገድ ላይ ነበር።

አስታውሱ፣ ሕዝቡ ድነትንና ስኬትን ፈልጎ ነበር። ይህ ማለት፣ መሲሑ ወደ ከተማዋ ዘምቶ ከሮም ጋራ ጠንካራ ጦርነት እንዲያደርግ ይፈልጉ ነበር። በታሪካቸው በሚገባ እንደተነገረው በኀይልም ቢሆን፣ በታላቅ ማስፈራትም፣ በመቅሠፍትም፣ ባሕርን በመክፈልም ቢሆን ከአሕዛብ ጭቈና ነጻ መውጣትን ፈልገው ነበር። ሮማውያንን የሚያስወጣ ሌላ ዘፀአት ፈልገው ነበር።

ከዚህ ይልቅ ግን፣ በዐርብ ጠዋት ያገኙት ደም የለበሰ፣ በሮማውያን ቊጥጥር ሥር የዋለ፣ በራሱ መሪዎች የተገፋ፣ በርባን ከተባለ መጥፎ ስም ካለው ወንጀለኛ አጠገብ የቆመ የተሸነፈ ሰው ነበር። ተወዳዳሪ የሌለው ንጉሥ ፈለጉ፣ ነገር ግን የተሸነፈ ችግር ፈጣሪን ተመለከቱ። ወይም እነርሱ ያሰቡት እንደዚህ ነበር።

በዚህ የሆሣዕና እሑድ የተሰማው የሕዝቡ ጩኸት፣ በዚያው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሚሰማው ሌላ የሕዝብ ጩኸት ይከዳል። “የተባረከ ነው!” የሚለው ብዙም ሳይቈይ “ስቀለው!” ወደሚለው ይለወጣል። በዚህ ምክንያት፣ ዛሬ በሚሆነው ነገር ውስጥ የሚያስጠላ ስሜት አለ። ለኢየሱስ የተሰጠውን ምላሽ እናነብባለን፣ ነገር ግን ታሪኩን ስለምናውቅ፣ ይህ የደስታ አቀባበል የመጨረሻው ቃል እንዳልሆነ እንገነዘባለን፣ ቢያንስ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች።

የእሑዱን ቃላት  ደስታና ውጤት አልባ የሆነውን ጕጕት ስናስብ፣ ዐርብ ዕለት የሚመጣውን ስድብ ከመስማት መቈጠብ አንችልም።

እነዚህን ሕዝቦች ማዳመጥ ብንችል ኖሮ፣ የእኛም ጩኸት ከእነርሱ ጩኸት ጋራ በአንድነት እንሰማው ነበር። የእኛን ምስጋና እንሰማለን፣ ከዚያም በዐርብ ዕለት፣ በሚያሳፍር መልኩ፣ “ከፌዘኞች ጋራ እየተሳለቅን” ፌዘኛ ድምፃችንን እንሰማ ነበር። በሕይወታችን ውስጥ በሆነ ወቅት፣ የሁለቱም ሕዝቦች አካል ሆነናል። ምናልባት እርሱን አሞግሰነው ይሆናል፤ ነገር ግን በሆነ ጊዜ እኛም አፌዘንበታል።

በመሠረቱ፣ ኢየሱስ ሊያድን የመጣው ጻድቃንን ሳይሆን፣ እንደ እኛ ያሉ ኀጢአተኞችን ነው።