የሆሣዕና እሑድ ጠዋት
“ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ የምትመጣዋ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም።” (ማርቆስ 11፥9-10)
የሆሣዕና እሑድ በቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የዘመን አቈጣጠር ውስጥ፣ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንት ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ጊዜ በባህላዊ መንገድ የምናከብርበት ቀን ነው።
ኢየሱስ በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በፍጹም ትሕትና ወደ ከተማዋ ሲገባ፣ ሊደርስበት ያለውን ነገር ያውቅ ነበር። ጠላቶቹ የበላይነትን ሊያገኙ ነበር፤ እርሱም ተቀባይነትን ዐጥቶ ሊሰቀል ነበር። ከተማዋ በአንድ ትውልድ ጊዜ (ማለትም ከ25-30 ባሉት ዓመታት) ውስጥ ፈጽማ ትጠፋለች። በሉቃስ 19፥43-44 ላይ ኢየሱስ ይህን እንዴት እንደ ተናገረው እንመልከት፦
“ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከብበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላወቅሽምና።”
እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ በኩል እየጐበኛቸው ነበር፤ “ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም” (ዮሐንስ 1፥11)። ነገር ግን የመጐብኘታቸውን ዘመን አላወቁም። ስለዚህም በማሰናከያው ድንጋይ ተሰናከሉ። ግንበኞች ድንጋዩን ናቁት፤ አውጥተውም ጣሉት። ኢየሱስ ግን፣ ይህ እንደሚመጣ አስቀድሞ አይቶ ነበር።
ንጉሡ አለቀሰ
ኢየሱስ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? “ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሯል” (ሉቃስ 19፥41-42)። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ዕውርነትና ሊመጣ ባለው መከራዋ ምክንያት አለቀሰ።
እነዚህን እንባዎች እንዴት ትገልጿቸዋላችሁ? እኔ የሉዓላዊ ምሕረት እንባዎች (tears of sovereign mercy) ብዬ እጠራቸዋለሁ። እነዚህ እንባዎች በእኛ ላይ ሊኖራቸው የሚገባው ተጽእኖ ክርስቶስን እንድናደንቅ፣ ከሌሎች ሁሉ በላይ እንድንወድደውና እንደ መሓሪ ሉዓላዊ ጌታችን እንድናመልከው ማድረግ ነው። እንዲሁም የምሕረቱን ውበት ባየን ጊዜ፣ ከርሱ ጋራ፣ እንደ እርሱና ለክብሩ መሓሪዎች እንሆናለን።
ስለዚህ፣ በዚህ የሆሣዕና እሑድ፣ ክርስቶስን ዐብረን እናድንቀው።
ርኅሩኅ ሉዓላዊነቱን ማድነቅ
ክርስቶስን እጅግ አስደናቂና ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተለየ የሚያደርገው፣ በሌሎች ሰዎች ዘንድ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ በርካታ ባሕርያትን በርሱ ውስጥ አጣምሮ መያዙ ነው። ፍጹም ሉዓላዊነትን መገመት እንችላለን፤ እንዲሁም ርኅራኄ የተሞላበት ምሕረትን ማሰብ እንችላለን። ነገር ግን መሓሪ ሉዓላዊነትን እና ሉዓላዊ ምሕረትን በፍጹም ተመጣጣኝነት አጣምሮ የያዘ ማንን መመልከት እንችላለን? ኢየሱስን እንመለከታለን። ሌላ የትኛውም ሃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ ተፎካካሪ ወደዚህ ደረጃ መጠጋት እንኳ አይችልም።
በሆሣዕና እሑድ ዘገባ ውስጥ ስለ ሉዓላዊነቱ የሚያሳዩ ሦስት ጠቋሚዎችን እንመልከት።
አንደኛ፣ ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ ታላላቅ ሥራዎች እግዚአብሔርን አመሰገኑ (ሉቃስ 19፥37)። ለምጽን በመንካት ፈውሷል፤ ዕውሮችን እንዲያዩ፣ ደንቈሮዎችን እንዲሰሙ፣ አንካሶችን እንዲራመዱ አድርጓል፤ ርኩሳን መናፍስትን አዝዟል፤ እነርሱም ታዝዘውለታል፤ ማዕበሎችን ጸጥ አድርጓል፤ በውሃ ላይ ተራምዷል፤ እንዲሁም ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን ለብዙ ሺሕ ሰዎች የሚበቃ ምግብ አድርጎ ባርኳል። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ፣ ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ያውቁ ነበር። እርሱ ቃል ቢናገር ጲላጦስ ሊጠፋ ይችላል፤ ሮማውያን ሊበተኑ ይችላሉ። እርሱ ሉዓላዊ ነበር።
ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ፣ በቊጥር 38 ላይ ተመልከቱ። ሕዝቡ፣ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስ ንጉሥ ነበር፤ ዝም ብሎ ማንኛውም ንጉሥ ሳይሆን፣ በጌታ እግዚአብሔር የተላከና የተሾመ ንጉሥ ነበር። ኢሳይያስ እርሱን፣ ፈጽሞ በማይሸነፍና ማለቂያ በሌለው መንግሥት ላይ ሉዓላዊ ገዥ አድርጎ እንደ ገለጸው ያውቁ ነበር፦
“ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።” (ኢሳይያስ 9፥7)
ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ቅንዓት የተደገፈ ዓለም ዐቀፋዊና ማለቂያ የሌለው መንግሥት። ዛሬ በሕዝቦችና በጋላክሲዎች ላይ የሚገዛው የዓለሙ ንጉሥ እዚህ ነበር፤ ለርሱ አሜሪካ፣ አይሲስ (ISIS) እና ማናቸውም ሌላ የፖለቲካ መንግሥት እንደ አሸዋ ቅንጣትና እንደ ትነት ብቻ ናቸው።
ሦስተኛው፣ ቊጥር 40 ላይ ይገኛል። ፈሪሳውያን ሕዝቡ እርሱን እንደ ንጉሥ አድርገው ማክበራቸውን እንዲያስቆም በነገሩት ጊዜ፣ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ብሎ መለሰላቸው (ሉቃስ 19፥40)። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ይመሰገናል! መላው የፍጥረት ንድፍ ክርስቶስ እንዲመሰገን ታስቦ የተሠራ ነው። ስለዚህ፣ ሰዎች ይህን ባያደርጉ፣ ድንጋዮች ይህን እንዲያደርጉት ያደርጋል።
በሌላ አነጋገር፣ እርሱ ሉዓላዊ ነው። ለማግኘት ያሰበውን ያገኛል። እኛ እርሱን ለማመስገን ፈቃደኞች ካልሆንን፣ ድንጋዮች ደስታውን ያገኛሉ።
ፍጻሜ እንጂ ውድቀት አይደለም
ስለዚህ፣ በቊጥር 41 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ እንባዎች፣ የርሱን ሉዓላዊነት ለመካድ ደጋግመው ጥቅም ላይ መዋላቸው አስገራሚ ነው። አንድ ሰው እንዲህ ሊል ይችላል፤ “ተመልከቱ፣ በእነርሱ ላይ ያለው ዐላማው ስላልተሳካ ለኢየሩሳሌም እያለቀሰ ነው። እርሱ እንዲድኑ ይፈልግ ነበር። ነገር ግን አሻፈረኝ አሉ። ሊክዱት ነው። እንዲሰቀል አሳልፈው ሊሰጡት ነው። ስለዚህ በእነርሱ ላይ የነበረው ዐላማው ከሽፏል።” ነገር ግን በኢየሱስ ሉዓላዊነት ላይ በሚነሣው በዚህ ተቃውሞ ውስጥ ልክ ያልሆነ ነገር አለ።
ከድንጋዮች ምስጋናን ማውጣት ከቻለ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት እንደ ድንጋይ ከጠነከሩ ልቦች ውስጥም እንዲሁ ማድረግ ይችል ነበር። ከዚህም በላይ፣ ይህ ሁሉ የኢየሱስ መገፋት፣ መሰደድና መገደል የዕቅዱ መክሸፍ ሳይሆን፣ የዕቅዱ መፈጸም ነው።
ከጥቂት ጊዜ በፊት በሉቃስ 18፥31-33 ላይ የተናገረውን አድምጡ፦
“ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ ነቢያት ስለ ሰው ልጅ የጻፉትም ሁሉ ይፈጸማል። ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል። እርሱ ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ይነሣል።”
ክሕደቱ፣ ፌዙ፣ ውርደቱ፣ ምራቅ መተፋቱ፣ ግርፋቱ፣ ግድያውና ሌሎችም በርካታ ነገሮች በዕቅድ የተያዙ ነበሩ። በሌላ አነጋገር፣ ተቃውሞው፣ ድንዳኔው፣ መገፋቱ፣ አለማመኑና ጥላቻው ለኢየሱስ ድንገተኛ አልነበሩም። እንዲያውም የዕቅዱ አካል ነበሩ። እርሱ ራሱ ይህን ተናግሯል።
በቊጥር 42 መጨረሻ ላይ፣ “አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሮአል” ያለው ለዚህ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ በሉቃስ 8፥10 ላይ ስለ ምሳሌዎቹ የተናገረውን አስታውሱ፦ “ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’” እግዚአብሔር ለልብ ድንዳኔ አሳልፎ እየሰጣቸው ነበር። ይህ ፍርድ ነበር።
መሓሪና ኀያል
የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ሉዓላዊ ምሕረት ነው። “የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ”(ሮሜ 9፥15)። ነገር ግን በሆሣዕና እሑድ የምናየው ነጥብ ይህ ነው፦ ይህ ሉዓላዊ ክርስቶስ ልባቸው ደንድኖ ዕቅዱን እየፈጸሙ ስላሉና ስለሚጠፉ የኢየሩሳሌም ሰዎች ያለቅሳል። የምሕረት እንባዎችን ከሉዓላዊነት ርጋታ ጋራ ማቃረን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና የተሳሳተ ተግባር ነው። ኢየሱስ በሐዘኑ ውስጥ የተረጋጋ፣ በሉዓላዊነቱም ውስጥ ያዘነ ነበር። የኢየሱስ እንባዎች የሉዓላዊ ምሕረት እንባዎች ናቸው።
ስለ ሆነም ሉዓላዊ ኀይሉ ይበልጥ የሚያስደንቅና ይበልጥ ውብ ነው። በውጥረት ውስጥ ያሉ የሚመስሉ ነገሮች ስምሙነት ክርስቶስን ክቡር ያደርገዋል፤ “መሓሪና ኀያል” ብለን እንደምንዘምረው ማለት ነው። ኀይልን መሓሪ ኀይል ሲሆን ይበልጥ እናደንቀዋለን። ምሕረትንም ኀያል ምሕረት ሲሆን ይበልጥ እናደንቀዋለን።
የክርስቶስን ውበት፣ ማለትም በሆሣዕና እሑድ የታዩትን የሉዓላዊ ደስታ እንባዎች፣ እንዲሁም በሕማማት ሳምንት ውስጥ እንዲጓዝ ያደረገውን ራስን አሳልፎ የመስጠት ፍቅርና ታዛዥነትን ብናይና ብናጣጥም ምንኛ መታደል ነው። በዚህ ሳምንት እርሱን ስናደንቀውና ስናመልከው፣ በምናየው ነገር ተለውጠን ይበልጥ ርኅሩኆች፣ ራሳችንን የምንክድና የሰዎችን ፍላጎት የምናሟላ ሰዎች ብንሆን እንዴት መልካም ነው።