ወደ ኋላ መመለስ የለም

የሕማማት ሰኞ ጠዋት

አንድሪያስ ኮስተንበርገር እና ጀስቲን ቴይለር (Andreas Köstenberger & Justin Taylor)

ከጠዋቱ 12፡30 ገደማ፣ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አንድ ማይል ተኩል ርቃ በምትገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ደቡባዊ ምሥራቅ ቁልቁለት ላይ ባለችው ትንሽ መንደር፣ ቢታንያ፣ ፀሓይ ወጣች። 33 ዓ.ም.፣ መጋቢት 30 (March 30) የሕማማት ሰኞ ነው። የናዝሬቱ ኢየሱስ ባረፈበት ትሑት ወዳጆቹ ቤት ይገኛል። እነርሱም፣ በጭንቀት የተሞላ መስተንግዶዋ የርሱን የዋህ ተግሣጽ ያስተናገደው ማርታ፣ መልካሙን ዕድል የመረጠችው ማርያምና የክርስቶስ ተአምራዊ ሥራ ባይኖር ኖሮ አካሉ አሁን በዚህ ወቅት በመቃብር ውስጥ ይሆን የነበረው አልዓዛር ናቸው።

ልክ በትላንትናው ዕለት፣ በሕይወቱ የመጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን፣ ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ የዘንባባ ቅርንጫፎችና ልብሶች በተነጠፈበት “ቀይ ምንጣፍ” ላይ በማለፍ የድል አድራጊነት ጕዞውን ወደ ቅድስቲቱ ከተማ አድርጎ ነበር። በደቀ መዛሙርቱና በገሊላውያን መንገደኞችም የመሲሐዊ ንጉሥ አቀባበል ተደርጎለት ነበር።

ነገር ግን ሰኞ ከእሑድ የተለየ ይሆናል። ኢየሱስ የሰውን ልብ ያውቅ ነበር (ዮሐንስ 2፥24-25)። የደቀ መዛሙርቱና የሕዝቡ አድናቆት የተገነባው በገዛ ራሳቸው የመሲሕነት ግንዛቤ ላይ እንደ ሆነ ያውቅ ነበር። በተደጋጋሚ በተቃራኒው ሊያስተምራቸው ቢሞክርም፣ የተሳሳተ ግምታቸውን ሊተዉ አልቻሉም። ይህም፣ የተጠሉትን ሮማውያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሚያስወግድ ብሔራዊ አዳኝ ጋራ የተያያዘው ዕሳቤ ነበር። ድል የሚመጣው ቊጣንና አሳፋሪ ውርደትን በሌሎች ላይ በማምጣት ሳይሆን ያንኑን በመቀበል (experiencing) ነው ለሚለው ሐሳብ ምንም ዐይነት ቦታ አልነበራቸውም።

ፍርድ ከቤት ይጀምራል

በማግስቱ ኢየሱስና ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከእንቅልፋቸው ነቅተው፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርጉት ዐጭር ጕዞ በተቀጣጠሩበት ስፍራ በቢታንያ ሲገናኙ፣ የኢየሱስ አጀንዳ ዛሬም እንደ ቀድሞው ተመሳሳይ ነበር፤ የርሱን ማንነትና ተልእኮውን በተመለከተ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማስወገድ ጥበቃዎቻችንና ግምቶቻችንን ማፍረስ ነበር። ይህ ዕለት ቀላልና ጸጥታን የተሞላበት ሰኞ አልነበረም። ኢየሱስ ፍርድ የሚጀምረው ከቤት፣ ከእስራኤል መሆኑን ሊያሳያቸው ነው።

በደብረ ዘይት ተራራ ዐለታማ መሬት ላይ ዐብረው ሲጓዙ፣ የኢየሱስ ራብ እየጨመረ ሲመጣ፣ ራቅ ብላ ያለች አንዲት የበለስ ዛፍን ተመለከተ። ከውጫዊ ገጽታዋ ስትታይ ጤናማ ትመስል ነበር፤ ፍሬ ፈልጎ ራቡን ለማስታገሥ የሚቻልባት ስፍራ ትመስል ነበር። ነገር ግን በቅርበት ሲመረምራት፣ ዛፏ ምንም ፍሬ ያልነበራትና ከማይበሉ ቅጠሎች በቀር ምንም ያልያዘች መካን ነበረች።

ኢየሱስ ቀጥሎ ያደረገውን ነገር፣ ደቀ መዛሙርቱ ፈጽሞ አልጠበቁትም ነበር። ከእንግዲህ ወዲህ ለዘላለም ፍሬ እንዳታፈራ በመግለጽ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ ርግማንን አወረደ (ማቴዎስ 21፥18-19ማርቆስ 11፥12-14)። ኢየሱስ ስለዚህ የሚታይ ምሳሌ በማግስቱ ያብራራል። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ዛፏን በመንፈሳዊ ዐይን ቢመለከቷት ኖሮ፣ በብሉይ ኪዳን እስራኤል በተደጋጋሚ፣ “የበለስ ዛፍ” በሚል ስያሜ ትጠራ እንደ ነበር ያስታውሱ ነበር (ኤርምያስ 8፥13ሆሴዕ 9፥10፣ 16ኢዩኤል 1፥7)። ፍርድ ከቤት መጀመር አለበት።

ቤተ መቅደሱን ማንጻት

በዚህ ያልተጠበቀ ድርጊት ደቀ መዛሙርቱ ሳይረበሹ እንዳልቀሩ እሙን ነው፤ ቢሆንም ጕዟቸውን ቀጠሉ። ኢየሱስ ግን ገና መጀመሩ ነበር።

በዚያው ዕለት ቈየት ብሎ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ ሲገባ፣ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ሃይማኖተኛ አይሁዳውያን ተከብቦ ነበር። እነዚህ ሰዎች የቤተ መቅደሱን ግብር (የጢሮስ ሰቅል) መክፈል ብቻ ሳይሆን፣ በአሕዛብ አደባባይ (Court of the Gentiles) ውስጥ ነውር የሌለበትን የመሥዋዕት እንስሳ መግዛት ነበረባቸው። ኢየሱስ ገንዘብ ለዋጮችንና ነጋዴዎችን ሲመለከት፣ ቅዱስ ቅንዓትና የጽድቅ ቊጣ በውስጡ ገነፈለ። ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት መሆን የነበረበትን (ኢሳይያስ 56፥7) የአባቱን ቤት፣ ምስኪን የፋሲካ መንገደኞችን የሚዘርፉበትና እውነተኛውን አምልኮ የሚያጣምሙበት የወንበዴዎች ዋሻ አድርገውት ነበር (ኤርምያስ 7፥11)። ኢየሱስ የገንዘብ ለዋጮቹን ጠረጴዛዎችና ወንበሮች መገልበጥ ጀመረ፤ ነጋዴዎቹንና የሚራወጡ ደንበኞቻቸውን አባረረ፤ ዕቃዎችን ለሽያጭ የተሸከሙ ሁሉ እንዳያልፉ ከለከለ።

እንደ ባልጩት ድንጋይ የጠነከረ ፊት

ከካህናት አለቆች፣ ጻፎችና ከአይሁድ መሪዎች አመለካከት አንጻር ሲታይ፣ ይህ ከገጠሪቱ ናዝሬት የመጣ አስተማሪ ታሪኮችን ሲያካፍል፣ ስለ ራሱ ሲናገርና ከተከታዮቹ ጋራ ተአምራቱን ሲያደርግ መቈየቱ አንድ ነገር ነው። አሁን ግን በቅድስቲቱ ከተማ ውስጥ ገብቷል። እንደ አዲሱ ዳዊት ወይም እንደ አዲሱ ሰሎሞን በበሮቿ ገብቷል። አሁን ደግሞ ቤተ መቅደሱ በመሠረቱ የርሱና የአባቱ እንደ ሆነ ለማወጅ ድፍረት አግኝቷል። የአይሁድ የአምልኮ ሥርዐት፣ አምልኮን ሳይሆን ኀጢአትን እያበረታታ ነው ለማለት እርሱ ማነው? የአይሁድ ባለ ሥልጣናት ስለ እውነተኛ አምልኮና እግዚአብሔርን መፍራት (godliness and piety) ምንም አያውቁም ብሎ ለመከራከር እንዴት ይደፍራል?

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላ መመለስ የለም። ኢየሱስ ወደ ኋላ እያፈገፈገ አይደለም። እንዲያውም፣ የሞት ፍርዱን እያፋጠነው ነው።

ምሽት እየቀረበ ነው። ፀሓይ ከምሽቱ 1፡00 (7:00 P.M.) ገደማ ትጠልቃለች፤ ይህም እንደ አይሁድ የቀን አቈጣጠር አዲሱን ቀን ያስጀምራል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቢታንያ ተመለሱ። ኢየሱስ ወደ ቀራንዮ የሚወስደውን የዘላለም ዕቅድ መፈጸሙን ሲቀጥል፣ ነገ ሰዎችን የሚያስገርምበትና ነገሮችን የሚገለባብጥበት አዲስ ቀን ይሆናል።