ደሙ በእኛ ላይ ይሁን

የሕማማቱ ቅዳሜ ጠዋት

የሕማማት ሳምንት፣ በዕለተ ቅዳሜ በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋና ጸጥታ የነገሠበት ነው። መቃብሩ ታትሟል፤ ጠባቂዎች ዘብ ቆመዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ በግራ መጋባት፣ በፍርሀትና ተስፋ በመቊረጥ ስሜት ተደብቀው ይሆናል። አዳኙ ደግሞ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ለማዳን ሁሉን ነገር አሳልፎ ሰጥቶ ሕይወት አልባ ሆኖ ተቀብሯል።

ባለፉት ሁለት ቀናት የተፈጸሙትን አስከፊ ክሥተቶችን በጸጥታውና በሚረብሸው የመስቀሉ ጥላ ሥር ሆናችሁ እንዴት ታስቧቸዋላችሁ? ደቀ መዛሙርቱ እልፍ የሚያሳምሙ ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ግድ ነበር። ከተገደለ፣ እንዴት እርሱ ለረጅም ጊዜ የተጠበቀው ንጉሥ ሊሆን ይችላል? ይህን ለማስቆም ልናደርገው የምንችለው ነገር ነበርን? እርሱን እንዲህ ካሠቃዩትና ካረዱት እኛን ምን ሊያደርጉን ነው? ቅዳሜን በሚጠብቁበት ጊዜ ይህ ሁሉ በአእምሯቸው ይመላለስ ነበር።

የሐሙስንና የዐርብን ጨለማና አሳሳቢ ማስተጋባት አሁንም እንሰማለን። ነገር ግን በነገው ዕለት ባዶውን መቃብርና የተነሣውን ንጉሥ በተስፋ እንጠባበቃለን። በተስፋ ተሞልተን ኢየሱስን ወደ ሰቀለው ሕዝብ ወደ ኋላ መለስ ብለን በማየት፣ አሮጌውን ማንነታችንን ልንመለከት እንችላለን። ከዚያም ወደ ፊት በመመልከት ለትንሣኤ በዓል እየተዘጋጀን፣ በመሥዋዕቱ ምክንያት በእኛ ውስጥ በተፈጠረው ለውጥ ደስ ይለናል። እነዚያን የመጀመሪያ ተከታዮች ግራ ባጋባቸው ደም እኛ ተሸፍነናል።

ኀላፊነት መውሰድ የተሳነው ጲላጦስ

ከእነዚህ ማስተጋባቶች አንዱ የሚመጣው ከማቴዎስ ምዕራፍ 27 ነው። ኢየሱስ ተከድቷል፤ ታስሯል፤ ተፈርዶበታል፤ እንዲሁም የሞት ቅጣት እንዲፈጸምበት ለገዢው ዐልፎ ተሰጥቷል። ማቴዎስ እንዲህ ይጽፋል፦

“አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያ ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር። ሕዝቡ እንደ ተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።” (ማቴዎስ 27፥15-18)

ጲላጦስ አንድን ወንጀለኛ ከሞት ፍርድ ነጻ የማውጣት ሥልጣን አለው። በፊቱ ታዋቂ ወንበዴ፣ ደግሞም ነፍሰ ገዳይ የሆነው በርባንና ኢየሱስ አሉ።

“ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር። አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ። እነርሱም፤ “በርባንን” በማለት መለሱ። ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጓል?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።” 

“ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ። ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።” (ማቴዎስ 27፥20-26)

“ደሙ በላያችን ይሁን” የሚለው ጩኸት

ይህ ቅንዓት፣ ጥላቻና አለማወቅ ነው። የእግዚአብሔርን ልጅ ለሞት አሳልፈው ለመስጠትና የታወቀን ነፍሰ ገዳይ ለማዳን እንዴት በዚህ ልክ ሊታለሉ፣ ሊጠመዘዙና ሊበላሹ ቻሉ? ጲላጦስ የጠየቁት ነገር ስሕተት መሆኑንና ኢየሱስ ደግሞ ንጹሕ እንደ ሆነ ያውቅ ነበር። በርሱ ግድያ ላይ ምንም ዐይነት ሚና ወይም ተሳትፎ እንዲኖረው አልፈለገም። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በአለማመን ተሞልተው፣ በዐመፀኛ ልብ፣ በገዛ መሲሐቸው ላይ በቅንዓት ቊጣ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” “ጲላጦስ አንተ ለመግደል ከፈራህ፣ ደሙ በእኛ ላይ ይሁን!” በማለት ጮኹ።

ደሙ በእኛ ላይ ይሁን? የእግዚአብሔር የራሱ ደም በእናንተ ላይ ይሁን? የዘላለም ሕያውና ፈጣሪ ቃል ደም በእናንተ ላይ ይሁን? አለማመናቸውና ቅንዓታቸው፣ ይኸውም ኀጢአታቸው፣ በእግዚአብሔር ላይ ወደ ማመፅና የመቃወም ድርጊት መራቸው። የርሱን ልጅ፣ የተስፋውን ቃል፣ ከዘመናት ዐመፅ ሊያድናቸው የላከውን ልጁን ሰቀሉት። ደሙ በእኛ ላይ ይሁን!

እርሱን እንዲሞት ያደረገው ኀጢአት ነው

ኀጢአት፣ ኢየሱስን መቃወም ነው፤ ይኸውም፣ እርሱ አሳሳች ወይም አታላይ ሰው ነው ብሎ ማወጅ ነው። እኛም በአለማመን ተሞልተን እግዚአብሔርን፣ ልጁንና መሥዋዕቱን ስንክድ የልባችን ሁኔታ ይኸው ነበር። በእምነት ማጣትና ባለመታዘዛችን፣ “ስቀለው!” ብለን ጮኸናል። ከሕዝቡ ጋራ በመሆን “እርሱ ንጉሣችን አይደለም!” “እርሱ መሲሓችን አይደለም!” “ደሙ በእኛ ላይ ይሁን!” ብለናል።

ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነና የተመረጡት ሕዝቦቹን  ስለሚታገሥ፣ “በክርስቶስ ፊት ያለውን የእግዚአብሔርን የክብሩን ዕውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ አብርቶአል” (2 ቆሮንቶስ 4፥6)። እርሱን በማመን ሕያዋን ሆነን፤ አዳኛችን የሞተበት መስቀል ላይ እናተኲራለን። ከኀጢአትና ከውጤቶቹ ይቅርታን ያገኘነውንና ነጻ የወጣነው በክቡር ደሙ ነው።

ተመሳሳይ መስቀል፣ አዲስ ጩኸት

ስለዚህ አሁን፣ ሙሉ በሙሉ በተለየ ትርጕም፣ ደሙ በእኛ ላይ ይሁን እንላለን። እርሱን እንደ ሰቀሉት ሰዎች በዐመፅ ሳይሆን፣ በመሥዋዕቱ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚደገፉ ሰዎች እጅግ አጥብቀን በመፈለግ፣ በምስጋና፣ በተስፋና በአምልኮ እንላለን። ኢየሱስ ሆይ፣ ደምህ በእኛ ላይ ይሁን። ይሸፍነን። ከራስህ፣ ከእጆችህ፣ ከእግሮችህ የሚፈስሰው ደም ይጠበን፤ እንዲሁም ከኀጢአታችን ሁሉ ያንጻን።

የኢየሱስን ሞት እናውጃለን። በሞቱ ደስ ይለናል፤ ይህን የምናደርገው አታላይ ወይም ዕብድ ነበር ብለን ስለምናምን ሳይሆን፣ በርሱ ሞት፣ በርሱ ቊስል፣ በርሱ ደም ስለ ተፈወስን ነው።