የመለወጥ አስተምህሮህ ውስጥ ኅብረት የተባለው መሠረታዊ ነገር ከሌለ፣ ከመላ አካሉ ዋነኛው ክፍል እንደ ጎደለ ያህል ነው። የኪዳኑ ራስ ከኪዳኑ ሕዝብ ጋር አብሮ የሚመጣ ነው።
አስቀድሞ ወደ ላይ፣ ቀጥሎ ወደ ጎን
ኅብረት ፊተኛውን ቦታ መያዝ አለበት እያልን አይደለም። አንድ ሰው መጽደቅ፣ “ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን የመሆኑን ያክል ስለ ነገረ ድነት አይደለም፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን የመሆኑን ያክል ድነት ተኮር አይደለም” በማለት የተናገሩትን የኤን. ቲ. ራይትን የታወቀ አባባል ሊያስብ ይችላል። “አዲስ ኪዳን ቅድሚያ የሰጠውን ኋላ ማድረግ፣ አዲስ ኪዳን ከኋላ ያሰፈረውን ደግሞ ፊት ማድረግ” የሚለው እውቅ የሆነ የዳግላስ ሙ አባባል ለዚህ ግልጽ ምሳሌ ይሆንልናል።
ኀጢአተኞች አስቀድመው ከእግዚአብሔር ጋር እስካልታረቁ ድረስ፣ ከሰዎች ጋር እውነተኛ የሆነ እርቅ ሊኖራቸው አይችልም። ‘ወደ ጎን’ ያለው ግንኙነት የግድ ‘ወደ ላይ’ ያለውን ግንኙነት ተከትሎ ይመጣል። ነገረ ቤተ ክርስቲያን የግድ ነገረ ድነትን ይከተላል። ለማለት የተፈለገው ኅብረት የተባለው ክፍል ቅድሚያ መሆን የለበትም፤ አለዚያ ሁሉን ማጣት ይሆናል።
ነገር ግን መከተል ይኖርበታል። በርግጥ ኅብረት የሚባለው ክፍል የመለወጥ[1] አስተምህሮ ውስጥ ሊኖር ይገባል። በክርስቶስ ያለን የኅብረት አንድነት የመለወጥ ምልክት ብቻ ሳይሆን ዋናው ክፍልም ነው። ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መታረቅ እና ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ማግኘት የሚለያዩ ነገሮች ቢሆኑም ሊነጣጠሉ ግን አይችሉም።
አንዳንዴ በመለወጥ (በድነት) አሠራር ላይ ትኩረት እየሰጠን ነገሩን ችላ እንለዋለን (ማለትም በአስተምህሮው ላይ ያሉ ውይይቶቻችን፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነትና በሰዎች ድርሻ ወይም የንስሓና እምነት አስፈላጊነት ላይ ብቻ የተገደቡ ይሆናሉ)። ቢሆንም ግን ስለ መለወጥ ሙሉ የሆነ መረዳት እንዲኖር ከተፈለገ ከየትና ወዴት እንደ ተሻገርን ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል። መለወጥ ከሞት ወደ ሕይወት መምጣትን፣ ከጨለማ አገዛዝ ወደ ብርሃን ግዛት መሻገራችንን ያካትታል። ከሰው አልበኝነት ወደ ሰው ማኅበር፣ ተቅበዝባዥ በግ ከመሆን ወደ መንጋው፣ ከአካሉ ከመነጠል ወደ አካሉ መቀላቀልን ያካትታል።
ከጴጥሮስ ንግግር ይሄን መመልከት ይቻላል:-
“እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥10)።
ምሕረትን (ከላይ የሆነ እርቅ) መቀበል ሕዝብ ከመሆን (ወደ ጎን ከሆነ እርቅ) ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ኀጢአታችንን ይቅር በማለት እግዚአብሔር ምሕረት አደረገልን፤ ሊቀር የማይችል ውጤቱ ደግሞ ወደ ሕዝቡ መቀላቀል ነው።
በቃል ኪዳኖች ውስጥ የኅብረት ተፈጥሮ
በርግጥ በመለወጣችን ውስጥ የሚገኘውን የኅብረት ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ካስቀመጠልን የቃል ኪዳን ምስል ውጭ ባለመመልከት፣ ነገሩን በሚገባ ማጤን እንችላለን። በብሉይ ኪዳን ያሉ ኪዳኖች ፍጻሜ የሚያገኙት በአብርሃም ዘር (ነጠላ) መሆኑ እውን ነው። ኢየሱስ አዲሱ እስራኤል ነው። ሆኖም በአዲሱ ኪዳን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆነ ሁሉ የእግዚአብሔር እስራኤልና የአብርሃም ዘር (ብዙ) መሆናቸውም እውነት ነው (ገላትያ 3፥29፤ 6፥16)።
በሌላ አነጋገር የኪዳኑ ራስ፣ ከራሱ ጋር የኪዳኑን ሕዝብ አብሮ ያቀርባል (ሮሜ 5፥12)። ስለዚህ በአዲሱ ኪዳን መካተት ማለት ወደ ሕዝብም መካተት ነው።
ስለዚህ በብሉይ ኪዳን የሚገኙ አዲስ ኪዳንን የሚያመለክቱ የተስፋ ቃሎች ስለ ሕዝብም ቃል የተገቡ ናቸው፦ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” (ኤርምያስ 31፥34)። አዲሱ ኪዳን የይቅርታን (ወደ ላይ) ተስፋ ይሰጠናል፤ ጨምሮም የወንድሞች ኅብረትን (ወደ ጎን) ተስፋ ይገባልናል።
“ወደ ጎን” እና “ወደ ላይ” በኤፌሶን 2
በሚገርም መንገድ ሙሉው ሐሳብ በኤፌሶን 2 ቀርቧል። ከቁጥር 1 እስከ 10 ስለ ይቅርታና ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ስላገኘነው እርቅ ሲያብራራ “በጸጋ ድናችኋልና” ይላል። ከቁጥር 11 እስከ 20 ወደ ጎን ስለ ሆነው ደግሞ ፦ “ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” ሲል ይናገራል (ቁ.14)።
የቁጥር 14 ክንውን በአላፊ ጊዜ ሰዋሰው የተቀመጠ መሆኑን ያስተውሏል። ክርስቶስ አስቀድሞ አይሁድና አሕዛብን አንድ አድርጓቸዋል። እዚህ ጋር ንግግሩ ትእዛዝ ተኮር አይደለም። ጳውሎስ ተደራሲያኑ አንድነትን እንዲፈልጉ እያዘዛቸው ሳይሆን ይልቁን አስቀድሞ የሆነን ነገር አመላካች በሆነ አነጋገር ያስረዳቸዋል። የሆኑትን የሆኑት እግዚአብሔር ከፈጸመው ሥራ የተነሣ ነው፤ ይሄን ሥራም የፈጸመው ደግሞ ወደ ላይ የሆነውን እርቅ በፈጸመበት በክርስቶስ መስቀል ነው (“አመላካች” (indicative) እና “ትእዛዝ” (imperative) በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በኤፌሶን 4፥1-6 ይመልከቱ)።
በክርስቶስ ከሆነው ከአዲሱ ኪዳን ባሕርይ የተነሣ፣ የኅብረት አንድነት የመለወጥ ምልክት ውስጥ የሚካተት ነው። መለወጥ ማለት በክርስቶስ አካል ውስጥ ብልት መሆን ማለት ነው። አዲሱ ማንነታችን ኅብረትን ያካተተ ነው። ክርስቶስ ኅብረትን ማዕከል ያደረጉ ግለሰቦች አድርጎናል።
ይህንን ለመረዳት ቀላል መንገድ እንጠቀም። እናትና አባት አንድን ልጅ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ወደ ማደጎ ቤት በሄዱ ጊዜ፣ ልጁን ወደ ቤት ይዘው መጥተው ከአዲስ ወንድሞችና እኅቶች ጋር እንዲሆን ወደ ቤተ ሰቡ እራት ግብዣ ያመጡታል። ልጅ መሆን ወንድም ከመሆን ጋር አንድ ዐይነት አይደለም። ልጅነት መቅደም አለበት። ነገር ግን ወንድምነት ይከተላል። ሊባል የተፈለገው መለወጥ ነው ወደ ቤተ ሰቡ የጋራ ፎቶ ውስጥ የሚያካትትህ።
የግል ተግባራዊ እርምጃ፦ ቤተ ክርስቲያንን መቀላቀል!
በእኛ ሕይወት እንዴት እንተግብረው? ቀላል ነው፦ በቤተ ክርስቲያን እንታቀፍ!
ጻድቅ ስለተደረግክ ጻድቅ ሁን። የአካሉ ብልት ሆነሃል፤ ስለዚህ የሚታየው አካል አባል ሁን። አንድ ተደርገሃል፤ ስለዚህ ከክርስቲያኖች ማኅበር ጋር አንድ ሁን።
የጋራ ተግባራዊ እርምጃ፦ አሠራሩ ላይ ትክክል መሆን!
ይህን ለቤተ ክርስቲያናችን እንዴት እንተርጉመው? ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በአስተምህሯችን ውስጥ ወሳኝ የሆነውን የመለወጥ አሠራርን በትክክል መረዳት ማለት ነው። ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነትና የሰዎች ድርሻ፣ ስለ ንስሓና እምነት ጠንካራ የሆነ እይታ እንዲኖረን እንፈልጋለን። ነገር ግን እዚህ ጋር ሚዛን ካልጠበቅን መጨረሻችን ብልሹ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ይሆናል። በመለወጥ ሳህን የምናስቀምጠው ያ የቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕድ ይሆናል።
የመለወጥ አስተምህሮህ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነት ጠንካራ አመለካከት ከጎደለው፣ ስብከትህና ወንጌል ስርጭትህም ጨቋኝና ሰውን ለማስደሰት የሚዳክር ይሆናል። በአመራር ጉዳይ ላይ የሚኖርህ መረዳት ተፃራሪ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ከአቅም በላይ የሆነ የፕሮግራም ሰሌዳ፣ ራስህንና ማኅበሩን አሸክመህ ለዝለት ትጋለጣለህ። የአባልነት ልምምዶችህ “የተለየ” ስምና ጥቅም ተኮር ይሆናሉ። ተጠያቂነትህና ሥርዐት ያለው ልምምድህ እየጠፋ መሄዱ አይቀሬ ስለሆነ፣ ቅድስናህ አደጋ ላይ ይወድቃል። እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል።
የመለወጥ አስተምህሮህ የሰው ድርሻን በተመለከተ ጠንካራ እይታ ከጎደለው፣ ለራስህም ለሌሎችም ስጦታ ባለ አደራ ከመሆን ትሰንፋለህ። የስብከት ዝግጅትና የወንጌል ስርጭትን ለመፈጸም ስትሠራ፣ ጥቅም ፈላጊ በመሆን ትፈተናለህ። ለተጎዱት ፍቅርና ርኅራኄ ከማሳየት ትጎድላለህ። በአጥባቂነት ወይም ዝግ ባለ መንፈስ ወደ ሌሎች መቅረብ ትጀመራለህ። ደካማ በሆነ የጸሎት ሕይወት ውስጥ በማለፍ፣ አላስፈላጊ መከራ ልትቀበል ትችላለህ፤ በዚህም ያንተ ሊሆኑ ከሚችሉ በረከቶች ትተላለፋለህ። ፍቅርን አደጋ ላይ ትጥለዋለህ። እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል።
የመለወጥ አስተምህሮህ ንስሓን በተመለከተ ጠንካራ ግንዛቤ ከጎደለው፣ ለሰዎች የድነትን እርግጠኝነት ለማቅረብ እየቸኮልክ ነገር ግን ክርስቶስን በመከተል ዋጋ እንዲከፍሉ ከማድረግ ትዘገያለህ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዓለማዊነትንና መከፋፈልን ችለህ ትቀመጣለህ፤ የቤተ ክርስቲያንህ አባላትም ከእምነታቸው ማነስ የተነሣ በእነዚህ ጉዳዮች አመቻምቸው እንዲቀመጡ ይሆናል። ጸጋም ስለሚረክስ ስም ብቻ ሆኖ የመቀመጡ ዝንባሌ ይስተዋላል። በጠቅላላው ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዓለም በማይለይ መልኩ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እንጂ ስለ ጌትነቱ መዘመር የማትወድ ትሆናለች።
የመለወጥ አስተምህሮህ እምነትን በተመለከተ ጠንካራ ግንዛቤ ከጎደለው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጭንቀት በሞላበት የራስን ጽድቅ ለማቆምና ሰውን ለማስደሰት በሚጥሩ ወግ አጥባቂዎች ትሞላለች። ራስን በመግዛት የተሻሉ የሚባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት፣ ራሳቸውን በማሳት ስለ ራሳቸው መልካም ነገር ሲያስቡ ራስን በመግዛት ያልተሻሉት አባላት ደግሞ ስውር ኀጢአታቸውን በመደበቅ ራስን በተደጋጋሚ መውቀስን ይለማመዳሉ፤ በዚህም ሌሎችን ቅር ያሰኛሉ። ግልፅነት እየደበዘዘ ግብዝነት ስፍራ እየያዘ ይሄዳል። የጠፉትና በውጭ ያሉት የእውነተኛውን ጸጋ ግለትና ርኅራኄ ሳይካፈሉ ይቀራል። እንደየባህሉ ልዩነት ያላቸው ነገሮች ከሕግ ጋር መምታት ይጀምራሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ክርስቶስ ጌትነት ለመስበክ እየበረታች፣ በደም የተለወሰውን በግ ለእርሷ እንደ ታረደ መዘመርን ትዘነጋለች።
እርግጥ ነው ሰፊ ሐሳብ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ነገሮች የዚህን ያክል ጥርት ባለ መስፈሪያ ላይገኙ ይችላል። ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች ውስጥ የተላለፈው ዋና ሐሳብ፣ በመለወጥ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ስላለው ጥብቅ ግንኙነት ያትታል። መለወጥ የግድ የኅብረትን ክፍል የሚያካትት ከሆነ፣ ወይም ጠንከር ባለ አነጋገር የግለሰብ መለወጥ ኅብረትን መመሥረቱ አይቀሬ ከሆነ፣ ከመለወጥ አስተምህሮህ ጋር የሚገናኝ ማንኛውም ነገር ምን ዐይነት ቤተ ክርስቲያን እንደምታገኝ ይወስነዋል።
ጤነኛ ቤተ ክርስቲያንን ትፈልጋለህ? በመለወጥ አስተምህሮህ ላይ በደንብ ሥራ፤ ለማኅበሩም የመለወጥ አስተምህሮ ሁሉን አቅጣጫ አስተምራቸው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንህ የሚደረጉ ፕሮግራሞች ብዙ መልክ ካለውና ጠንካራ ከሆነው ከዚህ አስተምህሮ ጋር አብረው እየተጓዙ መሆኑን አረጋግጥ።
ጆናታን ሊማን
[1] “Conversion” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።