መለወጥ (Conversion) ማለት ምን ማለት ነው?

መለወጥ[1] ማለት ሙሉ ለሙሉ የአቅጣጫ ለውጥ ማድረግ ማለት ነው። አንድ ሰው ከኀጢአት መንገድ ተመልሶ ለድነት ወደ ክርስቶስ ሲሄድ፣ ይህ ሰው ተለውጧል ማለት እንችላለን። ይህም ከጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ፣ ራስን ከማጽደቅ በክርስቶስ ወደ መጽደቅ፣ እንዲሁም ከራስ አገዛዝ ወደ እግዚአብሔር አገዛዝ መሻገር ማለት ነው።

በሰዎች ሕይወት ውስጥ መለወጥ የሚሆነው፣ ራሱ እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ሙታን የሆኑትን ሰዎች ሕይወት ሲዘራባቸውና ለንስሓ ሲያበቃቸው፣ እንዲሁም በክርስቶስ እንዲያምኑ ሲያስችላቸው ነው።

  • ኢየሱስ ንስሓ እንድንገባና እንድናምን ሲጠራን፣ ለውጥ እንዲሆንልን ጥሪ እያደረገልን ነው። ይህም በእምነታችንና በድርጊታችን ላይ ሥር ነቀል የሆነን ለውጥ ያመጣል። (ማርቆስ 1፥15)
  • ኢየሱስ መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው ሲጠራን፣ ለውጥ እንዲሆንልን ጥሪ እያደረገልን ነው። (ሉቃስ 9፥23)
  • በንስሓ መቅረብ እንችል ዘንድ፣ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወትን፣ አዲስ ልብን እና እምነትን ሊሰጠን ይገባል። (ኤፌሶን 2፥1ሮሜ 6፥17ቈላስይስ 2፥13ሕዝቅኤል 36፥26ኤፌሶን 2፥82ኛ ጢሞቴዎስ 2፥25)

መለወጥ ምን አይደለም?

  1. መለወጥ እንዴት መኖር እንዳለብን የማያሳይ የአንድ ጊዜ ብቻ ክስተት አይደለም። እርግጥ ነው መለወጥ በአንዲት ቅጽበት የሚከሰት ነገር ነው፤ ያም ደግሞ በሕይወታችን ሥር ነቀል የሆነን ለውጥ ያመጣል። ከዚያች ቅጽበት በኋላ ግን ሕይወታችን የተለየ መልክ ሊኖረው ይገባል። አዲስ ጦርነትም ይጀመራል።
  2. መለወጥ መዳረሻ የሌለው ጉዞ አይደለም። መለወጥ ለአንዳንዶች ረዘም ያለ ሂደትን ሊጠይቅ ይችላል፤ ነገር ግን ሁሌም ቆራጥ የሆነን ንስሓንና በክርስቶስ ማመንን ያካትታል። ይህም ራሱ እግዚአብሔር በኀጢአቱ ሙት ለሆነው ሰው ከሚሰጠው ሕይወት የሚመነጭ ነው።
  3. መለወጥ አማራጭ አይደለም። በሐዋርያት ሥራ 17፥30 ላይ፣ እግዚአብሔር በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ሲያዝዝ እንመለከታለን። መለወጥ በግድ እንዲከሰት ማድረግ አይቻልም፤ ሆኖም ግን ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው።
  4. መለወጥ ውይይት አይደለም። ክርስቲያኖች ወንጌልን ትሕትና በተሞላ መልኩ ለሌሎች መናገር ቢኖርባቸውም፣ ግባችን ግን አስደሳች የሆነን የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ብቻ አይደለም። ሰዎችን ሁሉ ከኀጢአታቸው ንስሓ እንዲገቡ እና በክርስቶስ በማመን ድነትን እንዲያገኙ መጥራት ይኖርብናል።
  5. መለወጥ የተቀመረ ጸሎትን ማነብነብ አይደለም። እርግጥ ነው መለወጥ ጸሎትን ያካትታል፣ ነገር ግን ሰዎች ልዩ በሆኑ የተወሰኑ ቃላት ላይ እምነታቸውን እንዲጥሉ እንዳንፈትናቸው ልንጠነቀቅ ይገባናል።

በብራድ ዊለር


[1] Conversion ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይሏል።