አስተምህሮ በድኻ ማኅበረሰብ ውስጥ አስፈላጊ ነውን?

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ከአንድ የድሮ የኮሌጅ ጓደኛዬ ጋር ቡና ለመጠጣት አብረን ተቀመጥን። ከተማሪነታችን ዘመን በኋላ፣ ለአገልግሎት ያለን አመለካከት ምን ያህል እንደተቀየረ ነገረኝ። ይህ ጓደኛዬ አሁን በተለያዩ ኮሌጆች ውስጥ በመሪነት እያገለገለ ይገኛል። ከዐሥራ አምስት ዓመት በፊት፣ እኔ እና እርሱ እንደ ነበርነው “መስቀል ተኮር” (እንደ እርሱ አነጋገር) ላለመሆን መወሰናቸውን እየነገረኝ ነበር። “ታውቃለህ ማይክ፣ ብዙም አስተምህሮ ላይ ማተኮር አንፈልግም። በርግጥ መስቀሉ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን በዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የስርየት ክርክር ውስጥ መግባት አንፈልግም። ደግሞም ኢየሱስ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ያሉ ብዙ ምሳሌዎችን በመጠቀም ስለ ድነት አስተምሯል። ለድኾች የምሥራች፣ ለታሰሩት ደግሞ ነፃ መውጣትን በመስበክ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋፋት እንፈልጋለን። የሚሠራ መልካም ሥራ አለ። ስለዚህ በነገረ መለኮት መጠመድ አንፈልግም።”

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጓደኛዬ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች ጋር ሊስማማ መቻል እና አለመቻሉን ለአፍታ ትቼ (ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በመካከላቸው ሳለ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ከሆነችው የእግዚአብሔር መንግስት ውጪ ሌላ እንዳያውቅ ወስኖ እንደ ነበርና… ቆይ ቆይ፣ ይህ ይቅር (1ኛ ቆሮንቶስ 2፥2) ሊያስተላልፍ የፈለገው ትልቁ ሐሳብ ምንድን ነው? በሐሳቡ ውስጥ በጎ ነገሮች አሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ ሊመጣ ካለው ጥፋት ለማስጠንቀቅ፣ ወደ ሩቅ ከተማ የምትጓዝ መርከብ ላይ ነህ እንበል። በጊዜ ካልደረስክ፣ በዚያ ስፍራ የሚገኘው ሰው ሁሉ ይሞታል፤ ስለዚህም ያለህበት መርከብ በተቻለ መጠን፣ በፍጥነት እንዲጓዝ ትፈልጋለህ። ፍጥነትህን ሊቀንስ የሚችል የትኛውንም ሸክም ከመርከቡ ላይ ታራግፋለህ። በመርከቡ ላይ ስላለው፣ ስለ ንጹሕ ወለል ወይም የተጣራ ናስ በመጨነቅ ጊዜህን አታባክንም። የሥራው አጣዳፊነት፣ በቅልጥፍና እና በአግባቡ መሥራትህን ይጠይቃል።

እንደ ጓደኛዬ ያሉ ሰዎች፣ የክርስቲያናዊ ተልእኮ አጣዳፊነት ነገረ መለኮታዊ ሸክሞቻችንንና ለአስተምህሮ ትክክለኝነት ያለንን ጭንቀት ማራገፍ እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። እንደዚህ ዐይነቱ ጭንቀት፣ አንድ ላይ መሥራት በሚገባቸው ሰዎች መሃል ጭቅጭቅን እና ግጭትን ያመጣል። ሰዎች እየተራቡ፣ ድኾች እየተጨቆኑ፣ ምርኮኞች በእስር ላይ እያሉ፣ መጽሐፍ መጻፍ፣ ኮንፍረንሶችን ማዘጋጀት እና በጥቂት ቃላት መከራከር ምን ይጠቅማል?

ይህ ትክክለኛ ሐሳብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ምርጫ ስለ ተከናወነበት ጊዜን በተመለከተ በኢንተርኔት ላይ ከሚከራከሩ ክርስቲያኖች ይልቅ፣ ለጎረቤታቸው ስለ ክርስቶስ የሚመሰክሩ ክርስቲያኖች ብትሞላ የተሻለ ነው። ይህ ማለት ግን፣ ድኾችን እና ችግረኞችን የምትፈልግ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥነ መለኮታዊ ውይይቶችን ማስወገድ አለባት ማለት አይደለም።

ዶክትሪን በመርከቡ ላይ ያለ ከባድ ጭነት አይደለም። የመርከቡ አካል እና ምሰሶ ነው።

የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ የምስክርነቷን ጸባይና ባሕርይን ይወስናል። የምትከተለው ነገረ መለኮት፣ ግቦቿን እና እነርሱን ለማሳካት የምትሄድበትን መንገድ ይቀርጻል።

ስለዚህ ጥያቄው ይህ ነው፦ ቤተ ክርስቲያን፣ ምዕመኖቿን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ፣ አስተምህሮን ማወቅ እና ማስተማር አለባት? የክርስቶስን ፍቅር በማሳየት እና ማኅበረሰባችንን በመርዳት ብቻ፣ እነዚህን መንትያ ግቦች ማሳካት እንችላለን? በዚህ ብቻ ማሳካት የሚቻል አይመስልም።

ይልቁንስ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው የትኛውም አገልግሎት አስፈላጊ ሆኖ እናገኛለን። ይህንን ለማሳየት ደግሞ የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት፦ ድነት እና መቀደስ

ለድነት፣ አስተምህሮ አስፈላጊ ነው

ከአስተምህሮ አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ ትችት የሚያቀርቡ አንዳንድ ሰዎች፣ በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር በሰዎች አእምሮ ውስጥ ሁሉም አስተምህሮአዊ ዕውቀቶች መኖሩን እንደማይመለከት ይናገራሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ሊጠይቃቸው ይችላል፦ ታምኑኝ ነበር? እውነተኛ የሆንኩትን እኔን ወይስ በእኔ ስም በተሠራ ሌላ እግዚአብሔር? በሌላ አነጋገር፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለ አስተምህሮ፣ ስለ ማንነቱ የሚናገር እውነት ስለሆነ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ እውነቶች እንድናምን ይፈልጋል።  

አንድ ሰው የክርስቶስን ማዳን እንዲያስተውል፣ በእውነተኛው እግዚአብሔር ማመን እና በእርሱ እውነቶች መደገፍ አለበት። አንድ ሰው በሙሉ ልቡ ወደ እግዚአብሔር ካልተመለሰ እና በእርሱ ካላመነ ሊድን አይችልም (ሮሜ 10፥13-17)። ለመዳን አስተምህሮ ያስፈልጋል!

ለዚህም ነው፣ ሐዋርያት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ሲሰብኩ፣ አስተምህሮአዊ መልእክቶችን ከማስተላለፍ ወደ ኋላ አይሉም ነበር። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ (እነርሱ እና ሌሎችም) ለማያምኑ ሰዎች ያስተማሩትን አስተምህሮአዊ ርእሶችን እንመልከት።

• ስለ መንፈስ ቅዱስ (2፥14-21)

• ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊ መግቦት (2፥2317፡26)

• ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ (2፥24–323፥15)

• የክርስቶስ ስቅለት (8፡32–3513፡28–29)

• እንዴት ብሉይ ኪዳን ኢየሱስን እንደሚያመለክት (3፥22–247፥2–5328፥23)

• ስለ መጪው ፍርድ እውነት (10፥4217፥3124፥25)

• ስለ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነት (4፥1219፥26)

• ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት (14፥15–1717፥24)

• ስለ እግዚአብሔር ሙሉነት (17፥24–25)

• ስለ እግዚአብሔር መንግሥት (19፥828፥23)

ሐዋርያት፣ ያላመኑ ሰዎች ወደ ክርስቶስ በእምነት እና በንሰሓ እንዲመጡ፣ ስለ እግዚአብሔር ማንነት እና በክርስቶስ ውስጥ ስለሚገኘው ድነት መረዳት እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል።

እንዲያውም ኢየሱስ፣ ተስፋ ቆርጦ ለነበረው ጳውሎስ በሕልም ሲገለጥ፣ እንዲህ ነበር ያለው፦ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” (የሐዋርያት ሥራ 23፥11)። ኢየሱስ የጳውሎስን አጠቃላይ የወንጌል አገልግሎት፣ ለአይሁድ እና ለአሕዛብ፣ ስለ እርሱ መመስከር እንደሆነ ይናገራል። ጳውሎስም ያደረገው ይህንኑ ነበር፤  ስለ ኢየሱስ ማንነት እና ስለ ሠራው ሥራ ከከተማ ወደ ከተማ እየዞረ ይመሰክር ነበር። 

“ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን የወንጌል ስብከት ኀላፊነት ለመወጣት፣ በቅድሚያ የተቸገሩትን መርዳት” ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ማስታረቅ ከባድ ነው። እውነታው ግን፣ ምንም ያህል ክርስቲያኖች፣ ለሺህ ዓመታት ሳሙና ቢያድሉ እና የሚያማምሩ ስዕሎችን ቢስሉ፣ ዓለም መቼም ቢሆን ኢየሱስ ለኀጢአቷ ሞቶ መነሣቱን አታምንም። በወንጌል ውስጥ ያለውን እውነት መናገር አለብን፤ አለበለዚያ ማንም አይድንም።

ቅድስና አስተምህሮ አስፈላጊ ነው

አንዳንዶች፣ ክርስቲያን ለመሆን መሠረታዊ አስተምህሮዎችን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ማመን ይከብዳቸዋል። ለክርስቲያናዊ ዕድገትም አብዛኞቹ “አስተምህሮዎች” አስፈላጊ እንዳልሆነ ያምናሉ። ይልቁንም በማኅበረሰባችን ውስጥ እንደ ኢየሱስ መኖርን ማስተማር አለብን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “አስተምህሮ አያስፈልግም” የሚለውን አመለካከት አያሳዩንም። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ በእውነተኛ አስተምህሮ ላይ ተደግፈው ትክክለኛ የሆነ እይታ እና ባሕርይ እንዲኖራቸው ያስተምራል።

እነዚህን ምሳሌዎች ተመልከት፡-

 • ዐሥርቱ ትእዛዛት። እንዴት መኖር እንዳለብን የሚነግሩን ከሁሉም የላቁ ትእዛዛት ናቸው። ከእነዚህ፣ እግዚአብሔርን በመምሰል ሕይወት ለመኖር ከተሰጡ መመሪያዎች በፊት ምን አለ? አስተምህሮ። “ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ” (ዘፀአት 20፥2)። እስራኤላውያን ለምን ሌሎች አማልክቶች አይኖሯቸውም? ምክንያቱም፣ ጌታ አግዚአብሔር ከባርነት ነፃ አውጥቶአቸዋል።

• ጠላቶቻችሁን ውደዱ። ይህ ትእዛዝ፣ ወንጌላችን ውብ እንዲሆን ያደረገ ትእዛዝ ነው። ነገር ግን፣ ልናስተውለው የሚገባው ኢየሱስ፣ የዚህ ፍቅር መሠረት አስተምህሮ እንደሆነ ይናገራል፦ “እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ። እንደዚህ በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል (ማቴዎስ 5፥44-45)። ለምን ጠላቶቻችንን እንወዳለን? ምክንያቱም አባታችን ጠላቱን የሚወድ አምላክ ስለሆነ ነው!

• ተቀደሱ። ክርስቲያኖች መቀደስ አለባቸው። ለምን? እንደገና ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ አስተምህሮ ይወስደናል፦ “ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” በአንድ ወቅት ይገዛን ከነበረ ክፉ ምኞት ጋር አሁን አንስማማም (1ኛ ጴጥሮስ 1፥14-15)።

• የጳውሎስ መልእክታት። በመጨረሻም፣ በጳውሎስ መልእክታት ውስጥ የሚገኙት ትእዛዛት፣ መሰረታቸው አስተምህሮአዊ እውነት ነው። ጳውሎስ የመልእክቱን ተቀባዮች፣ ሰውነታቸውን ሕያው መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ (ሮሜ 12፥1)፣ አዲሱን ሰው እንዲለብሱ (ኤፌሶን 4፥24)፣ በክርስቶስ እንዲኖሩ ያዛቸዋል (ቆላስይስ 2፥6)። ነገር ግን፣ እነዚህ ትእዛዞች የተሰጡት፣ ከረጅም አስተምህሮአዊ የሆኑ ትምህርቶችን በኋላ ነው። ጳውሎስ ለእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ስለ መጽደቅና መክበር፣ ስለ ተምሳሌትና ስለ ሰው ወኪሎች (ሮሜ 5፥12–17 8፥30)፣ ስለ ምርጫ እና አስቀድሞ መወሰን (ኤፌሶን 1፥4–6)፣ ስለ ሰው ልጅ ውድቀት (ኤፌሶን 2፥1–3)፣ እና ነገረ ክርስቶስ[1] (Christology) (ቆላስይስ 1፥15–20) አስተምሯል።

ክርስቲያናዊ ታዛዥነት፣ ለተቸገሩት ዋጋ ከፍሎ መድረስን ጨምሮ፣ የእግዚአብሔር ማንነት እና ሥራን መልሕቅ ማድረግ አለበት። ይህ መልሕቅ ሲነሣ፣ ለተወሰነ ጊዜ በቦታው ልትቆይ ትችላለህ፣ ነገር ግን ነፋስ እና ወጀብ ሲመጣ፣ ከቦታህ ያንቀሳቅስሃል። ለሌሎች ዋጋ መክፈልም፣ ያበቃል።

እግዚአብሔርን ይበልጥ ባወቅነው ቁጥር፣ እርሱን በመታዘዝ እናድጋለን። ምን ያህል ሰዎች በቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ እየጸለዩ፣ እውነተኛውን የእምነትን አስተምህሮ ስላልተማሩ፣ በታዛዥነት ማደግ ተስኗቸዋል? ምን ያህሉ ክርስቲያንስ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ እና በእርሱም ሕይወት ስለሚኖረው አንድምታ ባለማወቅ በራስ ወዳድነት፣ በስንፍና እና በኀጢአት ውስጥ ተዘፍቆ ይገኛል?   

ግን ቆይ . . .

ከጊዜ ወደ ጊዜ የምሰማው ሌላ ሐሳብ ደግሞ፣ “ድኻ ማኅበረሰቦች ጥራት ያለውን ትምህርት ለመማር ዕድሉ ስለሌላቸው፣ አስተምህሮዎችን ለመማር አስፈላጊው የመማሪያ መንገድ የላቸውም” የሚል ነው። ማንበብ እና ማጥናት ባህል ባልሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች፣ የተወሳሰበ ነገረ መለኮታዊ ሐሳቦችን ማስረዳት አይቻልም። ለማስረዳት መሞከርም፣  የማወቅ ፍላጎታቸው የበለጠ እንዲቀንስ ማድረግ ነው። እንዲህ ያለው አመለካከት፣ እነዚህን ሰዎች ማሳነስ ነው ብዬ አስባለው። ድኻ ሰዎች፣ ድኻ እንጂ መረዳት የማይችሉ ሰዎች አይደሉም። እንደ ማንኛውም ሰው፣ ስለ እግዚአብሔር ማንነት እና ስለ እርሱ አሠራር መረዳት ይችላሉ። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለምሁራን አይደለም። አንባቢዎቹ ባለጸጋ እና የተማሩ ሰዎች አልነበሩም። እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ የነገረ መለኮት ዲግሪ አልነበራቸውም። ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ራሱ ጥልቀት ያለውና የተወሳሰቡ እውነቶችንም ነግሮአቸዋል።

ድኾች ጥልቅ እውነቶችን መረዳት ይችላሉ። ይህንን በአሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገለግልበት ጊዜ፣ እንዲሁም በኤድንበርግ በምሠራበት ጊዜ አይቻለሁ።

ጎርደን የሚባል አንድ ሰው አለ። ዕድሜው በአርባዎቹ መጀመሪያ ነው። ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አልጨረሰም፤ እንዲሁም ምንም መጽሐፍ አንብቦ አያውቅም። ስለ ክርስትናም ሆነ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዐይነት ቅድመ ግንዛቤ አልነበረውም። ማንበብ ብቻ ይችላል። ወደ ሜዝ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጣ በኋላ፣ ትምህርቱን ለመረዳት እጅግ እንደ ከበደው ተናግሯል። የእርሱን ቃላት ላስቀምጥ፦

“ከመዳኔ በፊት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚናገር መረዳት አልችልም ነበር። አሁን ግን ስሜን እየጠራ ወደ ራሱ እንደሚስበኝ ይሰማኛል። ይሄ መንፈስ ቅዱስ ይመስለኛል። ከዚህ በፊት አስቤ በማላውቅባቸው መንገዶች፣ የሕይወትን ጥልቅ ጥያቄዎችን እንዳስብ አድርጎኛል። አሁን፣ አዘውትሬ ማንበብ እፈልጋለሁ። ነገረ መለኮታዊ የሆኑ ቃላት ባገኝም፣ ለመማር ግን ዝግጁ ነኝ። እግዚአብሔርን ይበልጥ መውደድ እፈልጋለሁ። እርሱንም ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ። ሳያሳቅቁ የሚያብራሩልኝ መልካም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንድረዳ እጅግ ጠቅመውኛል። ትምህርት ቤት እያለሁ አንድ ነገር ከከበደኝ፣ ቶሎ ተስፋ እቆርጥ ነበር። አሁን ግን እጅግ ለመረዳት የሚከብዱኝ ነገሮች ቢኖሩም፣ በጽናት እና በትዕግሥት እየተማርኩ ነው።”

ጎርደን ከመዳኑ በፊት የሙሉ ጊዜ ሥራን መሥራት አይችልም ነበር። የዕፅ ሱሰኛ ሆኖ በተመሰቃቀለ ሕይወት ውስጥ ይኖር ነበር። ከሁለት ደቂቃ በላይ መቀመጥ አይችልም። አሁን ግን የአርባ ደቂቃ ስብከት ቁጭ ብሎ ያዳምጣል። ባገኘውም አጋጣሚ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይፈልጋል።

ያልተማሩ እና ማንበብ የማይችሉ ሰዎችን አሳንሰን ማየት የለብንም። ሙሉ በሙሉ ማንበብና መጻፍ ከማይችሉ ወይም የአእምሮ ጤና ሕመም ካለባቸው ሰዎች ጋር የምትሠራ ከሆነ፣ የምታስተምርበትን ዘዴ ማስተካከል ይኖርብሃል። ሁሉም ጥሩ አስተማሪዎች፣ የሚሰጡትን ትምህርት ለሰሚዎቻቸው እንዲሆን በማድረግ አቀራረባቸውን ያስተካክላሉ። እስካሁን ባለን ቆይታ ድኾች ሊረዱት የማይችሉት አስተምህሮ አልገጠመንም። አስተምህሮውን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ተደግፈን ግልጽ በሆነ መልኩ፣ በደንብ ማስተማር ከቻልን፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሊማረው እና በእርሱም ሊያድግ ይፈልጋል።

ማጠቃለያ

በአስተምህሮዎች ማመን እና እነርሱንም ማስተማር፣ የወንጌል ሥርጭት እንዳይካሄድ ይከለክላል? አይከላከልም። እንዲያውም አስተምህሮዎችን ካላስተማርን፣ ለክርስቶስ የሚታዘዙ ደቀመዛሙርት የማድረግ ተልእኮአችንን መወጣት አንችልም። ክርስቶስን በመውደድ፣ ድኾችን መርዳት ብቻ በቂ አይደለም። ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንክሮ መሥራት ብቻ በቂ አይደለም። የወንጌሉን እውነት መናገር አለብን። አለበለዚያ ለራሳችን ብቻ ክብር እናመጣለን። እነርሱንም ለኀጢአታቸው እንተዋቸዋለን።

*****

የአርታዒ ማስታወሻ፡ ይህ አጭር ጽሑፍ “Church in Hard Places” ከተሰኘው በ2016 እ.ኤ.አ የታተመው ከማይክ እና ሜዝ አዲስ መጽሐፍ፣ በCrossway, a publishing ministry of Good News Publishers ፈቃድ የተወሰደ ነው።

ሜዝ ማክኮኔል እና ማይክ ማክኪንልይ


[1]