ስለ ሲኦል[1] ማሰብ ማንን ደስ ያሰኘዋል? እንዲያውም “ስለ ሲኦል ከማሰብ ይልቅ ስለ ሌላ ማንኛውም ነገር ማሰብ የተሻለ ነው” እንድንል ከሚያስገድዱን ርዕሶች አንዱና ዋነኛው አይደለምን? ለአንዳንዶች እንዲያውም የክርስትና አስተምህሮ የሆነው ትምህርተ ሲኦል እና የትምህርቱ አስፈሪነት (ማለትም ሲኦል ዘላለማዊ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሁሉ በሙሉ ማንነታቸውና በሙሉ ንቃታቸው በማያቋርጥ ስቃይ የሚሰቃዩበት ቦታ መሆኑ)፣ ስለ እርሱ ማሰብን ወደ መሸሽ ብቻ ሳይሆን ከናካቴው ሲኦል የሚባል ነገር የለም ብሎ ወደ መደምደም የክህደት ጫፍ አድርሷቸዋል። ብዙዎች፣ “በርግጠኝነት ሲኦል የሚባለው ነገር ሰዎችን በፍርሀት ቀፍድዶ ለመያዝ ሆን ተብሎ የተፈበረከ የሰዎች የልብ ወለድ ፈጠራ መሆን አለበት እንጂ፣ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር እንዲህ የመሰለው የስቃይ ቦታ እንዲኖር ፈጽሞ አይፈቅድም!” ሲሉ ይደመጣል። በርግጥ ይህ ሙግት ስሜታችንን የመግዛት አቅም እንዳለው ግልጽ ነው። ማንም ሰው (ክርስቲያንም ጭምር) ሲኦል መኖሩን ማወቁ እና ሰለ ሲኦል ማሰቡ ደስ አያሰኘውም፤ ሲኦልንም የሚወድ ማንም የለም።
ሆኖም ግን፣ ይህ አስተምህሮ በክርስትና የእምነት ማዕቀፍ ውስጥ ቢኖርም ባይኖርም ለውጥ የማያመጣ፣ ለክርስትና እምነት መቆም አዕማድ ከሆኑት አስተምህሮዎች የማይቆጠር እና እዚህ ግባ የማይባል ቅጥያ ትምህርት አይደለም። በተጨማሪም ትምህርተ ሲኦል አሳፋሪ፣ አላስፈላጊ፣ ኋላ ቀር እና እመኑ ስለተባልን ብቻ እንዲሁ በጭፍን የምናምነው ከንቱ ነገርም አይደለም።
እንዲያውም በተቃራኒው፣ የሲኦል እውንነት እና አስተምህሮ የወንጌልን ክብር ጥርት አድርገን ማየት እንድንችል የሚረዳን መልካም ማንጸሪያ ነው። እግዚአብሔር ምንኛ ታላቅ እንደሆነ፣ እኛ ደግሞ ምንኛ በኀጢአት የከረፋን ከንቱዎች እንደሆንን እና እግዚአብሔር ለእኛ ለኀጥኣኑ ጸጋን ለመስጠት መፍቀዱ ምን ያህል አስደናቂ ነገር መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል። በተጨማሪም ከአእምሮአችን ውስጥ አሽቀንጥረን ካላወጣነው በቀር ሲኦል እውን መሆኑን ማወቃችንና ማመናችን፣ በሕይወታችን ዋጋ ከምንሰጣቸው ከማናቸውም ነገሮች በላይ ለዘላለም በሲኦል በስቃይ ለመኖር ጉዞ ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ ወንጌልን ለመመስከር በመትጋት ላይ እንድናተኩር ያደርገናል።
ይህንን ለመግቢያ ከተነጋገርን በመቀጠል ለምን ትምህርተ ሲኦል የወንጌል ዋነኛ ከሚባሉት ክፍሎች አንዱ እንደሆነ የሚያስረዱ አምስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን እንመልከት።
ለምን ሲኦል የወንጌል ቁልፍ ክፍል ሆነ?
ምክንያቱም፡-
1. ሲኦል የሚባል እውነተኛ ቦታ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል
ይህንን ነጥብ ለማብራራት ብዙ መድከም አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም። ሌሎች ብዙ ጸሐፊዎች ይህንን ሐሳብ አስፋፍተውና አጥርተው አስረግጠውታል። በአሁኑ ጊዜ ላሉ ሰዎች የመካከለኛው ዘመን ቀሳውስት፣ ሐዋርያት፣ ወይም ኢየሱስ ራሱ ከሌሎች የተዋሱት አልያም የፈበረኩት ፈጠራ አለመሆኑን ማስተዋሉ በቂ ነው። የመካከለኛው ዘመን ቀሳውስት፣ በዘመናቸው የነበሩትን ጭሰኞች ለማስፈራራት ትምህርተ ሲኦልን አልፈበረኩትም፤ ነገር ግን ከሐዋርያት ተቀብለው አስተምረውታል። ሐዋርያት ደግሞ በእነርሱ ዘመን የነበሩትን አረማውያን ለማስደንገጥ ሲኦልን አልፈጠሩትም፣ ነገር ግን ከራሱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰምተው አስተምረውታል። ኢየሱስ ክርስቶስም ከቀደመው የዞራስትራውያን ፍልስፍና ቀድቶ የዘመኑን ፈሪሳውያን ለማስፈራራት ሲኦልን አላስተማረም። ነገር ግን እርሱ እግዚአብሔር ነበረ። ስለሆነም ሲኦል የሚባል ቦታ መኖሩን ያውቃል፤ ማንም እንዲያስተምረው አያስፈልገውም። ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ከኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ ሲኦል መኖር በግልጽ ተጽፎ ይገኛል።
ስለዚህ ክርስትያን ነን የምንልና መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን የምናምን ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሲኦል እውን መሆኑን እንደሚያስተምር ዕውቅና ከመስጠት መጀመር ይኖርብናል። ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ነገር ግን ተጨማሪ አለ።
2. ሲኦል ኀጢአታችን ምን ያህል አስከፊና አስቀያሚ እንደሆነ ያሳየናል
አንዳንድ ሰዎች “የትኛዉም ዐይነት ኀጢአት ዘላለማዊ የሲኦል ስቃይ አይገባዉም” ብለው ሲከራከሩ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? የሰዎች ልብ ምን እንደሚመስል ብዙ የሚናገር አስገራሚ የመከራከሪያ ነጥብ ነው። ለምንድን ነው ሰዎች ስለ ሲኦል ሲያስቡ እግዚአብሔር እንደ ተሳሰተ እንጂ እነርሱ እንዳልተሳሳቱ አድርገው ሁልጊዜ የሚደመድሙት? ምን ያህል ይህ አስተምህሮ ልባችንን ገልጦ እንደሚያሳየን ለማስተዋል ትችላላችሁ። የየራሳችንን ኀጢአት ስንመዝን ሁልጊዜ የመጀመሪያው ዝንባሌያችን፣ ኀጢአታችንን አሳንሰን ማየት ነው፤ ደግሞም እግዚአብሔር ኀጢአታችን ክፉ ነው ባለው መጠን እንደማይከፋና እግዚአብሔር ኀጢአታችን ቅጣት ይገባዋል ብሎ በመወሰኑ እንደተሳሳተ አድርገን በማሰብ የእግዚአብሔርን እውነት እንቃወማለን።
የሲኦል እውንነት ያን የራስ ጽድቅ የሚያፈርስ ትልቅ ተቃውሞ/ሙግት/ ሆኖ ይቆማል። ክርስትያን ያልሆኑ ሰዎች የሲኦልን አስፈሪነትና ሰቆቃ የተሞላበት ቅጣት ሲያስቡ፣ እግዚአብሔርን ክፉ ነው ብለው ለመክሰሻ ምክንያት አድርገው ያቀርቡታል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጻድቅነትና ፍጹም ፍትሐዊነት የምናውቅ ክርስትያኖች፣ የሲኦል አስፈሪነት እና የቅጣቱ ከባድነት በእኛ ላይ እግዚአብሔር ያቀረበው ክስ ምን ያህል ከባድ መሆኑን እንደሚያስረዳ ማስተዋል አለብን። የተጣለብን እጅግ አስፈሪ ቅጣት እኛ ምን ያህል ጥፋተኞች እንደሆንን ያሳያል። ኀጢአታችንን ልናሳንስ፣ ልናስተባብል፣ ወይም የሚወቅሰንን የራሳችንን ኅሊና ዝም ለማሰኘት እንሞክር ይሆናል። እውነታው ግን ለኀጢአቶቻችን እግዚአብሔር የዘላለም ስቃይ እንደሚገባን መፍረዱ፣ ኀጢአቶቻችን እኛ እንደምንገምታቸው ቀላል እንዳልሆኑ ሊያስታውሰን ይገባል። ኀጢአቶቻችን እጅግ ከመጠን በላይ ክፉዎች ናቸው።
3. ሲኦል እግዚአብሔር የማይለወጥ እና ስሕተት አልባ የሆነ የፍትሕ አምላክ መሆኑን ያሳየናል
በታሪክ ውስጥ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ለወደደው ሰው የፍትሕን ጥያቄ ገሸሽ በማድረግ፣ አድልዎ እንደሚያሳይ ሙሰኛና ኢ-ፍትሐዊ ዳኛ አድርገው ለመመልከት ተፈትነዋል። “እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን!” በማለት “እንዴት እግዚአብሔር ይህን የመሰለ አሰቃቂ ፍርድ በአንዳንድ ልጆቹ ላይ ይበይናል?” የሚል መከራከሪያ ይቀርባል። ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፦ እግዚአብሔር ፍትሕ የሚያጣምም ፍርደ ገምድል ዳኛ አይደለም! እርሱ እውነተኛ፣ ጻድቅና ፍጹም ፍትሐዊ ዳኛ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ነጥብ ደግሞ ደጋግሞ ያስረግጣል። እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ ሲገልጽለት ርኅሩኅና መሐሪ እንደሆነ ይናገራል፤ ነገር ግን በዛው ትንፋሽ “በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ” (ቀ.ኃ.ሥ.ት)[2] የሚል ኀይለ ቃል ይጨምራል። መዝሙራት ደግሞ “የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው” (ቀ.ኃ.ሥ.ት) በማለት ይመሰክራሉ። እንዴት የሚገርም አገላለጽ ነው!? እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ የሚቀጥል ከሆነ ፍትሕን እንዲሁ ገሸሽ አድርጎ ኀጢአትን በዝምታ አያልፍም። ነገር ግን ኀጢአትን በማያዳግም፣ ትክክል እና ተመጣጣኝ በሆነው ፍርዱ ይቀጣዋል። እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን በሚፈርድበት ጊዜ፣ አንድም ኀጢአተኛ ከሚገባው በላይ ወይም ከሚገባው በታች ፍርድና ቅጣት አይቀበልም፤ ሁሉም ለየሥራው የሚገባውን ተመጣጣኝ ቅጣት ይቀበላል።
እግዚአብሔር ጠላቶቹን በፍርድ ቀን ወደ ሲኦል በሚልክበት ጊዜ፣ መላ ዓለሙ ይህ የእግዚአብሔር ውሳኔ እውነተኛና ፍትሐዊ መሆኑን እንደሚገነዘብ እና ዕውቅና እንደሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 5 ይህንን ሐሳብ በግልጥ ያስረዳል፦ “ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች” (ቀ.ኃ.ሥ.ት)። የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ሁሉ ለመዋጥ መቃብር አፉን አስፍቶ እየጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ከባድና አስፈሪ አገላለጽ ነው። ነገር ግን ነብዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ይህን ፍርድ በሕዝቡ ላይ በመፍረዱ ፍትሐዊነቱን እንዳሳየ እንዲህ ሲል ይመሰክራል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ብሎአል፥ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ተቀድሶአል” (ቀ.ኃ.ሥ.ት)። በተመሳሳይ ቅዱስ ጳዉሎስም በሮሜ 9፥22 ላይ እግዚአብሔር በሲኦል አሰቃቂ ፍርድ አማካኝነት “አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ” (ቀ.ኃ.ሥ.ት) ለጥፋት በተዘጋጁት የቁጣ ዕቃዎች ላይ ቍጣውን ያሳያል፣ ኀይሉንም ይገልጣል ይለናል። ይህ ማለት የሲኦል ፍርድ የእግዚአብሔርን ኀይልና ቁጣ የማሳያ፣ ምሕረት ለሚደረግላቸው ሰዎች ደግሞ የተደረገላቸውን ምሕረት አጉልቶ የሚያሳይበት ልዩ መሣሪያው ነው ማለት ነው።
ምንም እንኳን አሁን ሙሉ በሙሉ ልንረዳው ባንችልም፣ አንድ ቀን ግን ሲኦል ራሱ የእግዚአብሔርን ክብር ይመሰክራል። ሲኦል ምንም ያህል አሰቃቂ፣ አሰቀያሚና አሰፈሪ ቢሆንም፣ ራሱ ሲኦል ከዘማሪው ጋር “የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው” (ቀ.ኃ.ሥ.ት) በማለት በአንድነት የሚመሰክርበት ቀን ይመጣል።
4. ሲኦል መስቀሉ ምን ያህል አሰቃቂ እንደነበር እና የእግዚአብሔር ጸጋ ምነኛ ታላቅ እንደሆነ ያሳያል
የሮሜ መልእክት ምዕራፍ 3 እግዚአብሔር ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ኢየሱስን የኀጢአት መሥዋዕትና ማስተሰረያ አድርጎ እንዳቀረበው ይነግረናል። ይህንን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ “ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ” (አ.መ.ት)[3] በትዕግሥት አልፎ ስለነበር ነው።
ኢየሱስ ለምን በመስቀል ላይ መሞት አስፈለገው? ምክንያቱም እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን በእውነተኛ ጽድቁ ምክንያት ወደ ሲኦል እንዳያወርደን የነበረው ብቸኛ መንገድ እርሱ ብቻ ስለነበር ነው። እኛ ከሲኦል ፍርድ እንድንተርፍ፣ ኢየሱስ ለእኛ የተገባውን ቅጣት መውሰድ ነበረበት። ያ ማለት ደግሞ ሲኦል ውስጥ አንድ ሰው ሊቀጣ የሚችለውን ከፍተኛውን የሲኦል ቅጣት ኢየሱስ በመስቀል ላይ በተንጠለጠለበት ጊዜ መቀበል ነበረበት ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ኢየሱስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነበር ማለት አይደለም። ነገር ግን የምስማር ችንካሮቹ፣ የእሾህ አክሊል፣ በአጠቃላይ የአካሉ ስቃይ፣ ኢየሱስ በመስቀል ከተቀበለው አጠቃላይ መከራ የመጀመሪያዎቹ ብቻ ነበሩ። እውነተኛ የሆነው የስቃዩ ክብደት የነበረው እግዚአብሔር በኀጢአት ላይ የነበረውን ሙሉ ቁጣ በላዩ ላይ ሲያፈስበት የተሸከመው ስቃይ ነው። አንዳንዶች እንደተናገሩት በመስቀሉ ጊዜ ምድርን የሸፈናት ጨለማ፣ እግዚአብሔር የልጁን ስቃይ መሸፈኑን ለማሳየት የመጣ አልነበረም። ያ ጨለማ የእርግማን ጨለማ ነበር፤ የእግዚአብሔር የቁጣው ጨለማ፤ የሲኦል የራሱ ሙሉ ጨለማ። በእነዚያ ሰዐታት ደግሞ ኢየሱስ የሁሉን ቻዩን የእግዚአብሔርን ሙሉ የቁጣ ወላፈን እየተቀበለ ነበር።
ክርስቲያኖች ከሆናችሁ መስቀሉን በዚህ መልኩ ማየት ስትጀምሩ፣ ለእናንተ የተሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ምን ያህል የከበረ መሆኑን በተሻለ መንገድ መረዳት ትጀምራላችሁ። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ተቀብሎት የመጣው የማዳን ተልእኮ የእግዚአብሔርን ቁጣ በእናንተ ቦታ ሆኖ የመሸከም የግዴታ ውልን ያጠቃልላል። ይህ ግዴታ ለእናንተ የሚገባውን ሲኦልን የመውሰድ ግዴታ ነው። እንዴት የሚያስገርም ፍቅርና ምሕረት ነው!? ነገር ግን ይህንን ፍቅር አጥርታችሁ ማየትና መረዳት የምትችሉት ሲኦልን ስትረዱት፣ ስትቀበሉት እና ከክርስቶስ ውጪ ብትሆኑ ሲኦል እንደምትገቡ በማወቅ እውነተኛው ፍርሀት ሲሰማችሁ ብቻ ነው።
5. ሲኦል ትኩረታችንን ወንጌልን በመስበክ ላይ እንድናደርግ ያስችለናል
ሲኦል በርግጥ ካለ፣ እንዲሁም ሰዎች በእውነት ዘላለማቸውን እዚያ ለማሳለፍ በአደጋ ውስጥ ከሆኑ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ አስቀድሞ ለሐዋርያቱ እንዲያደርጉ ከነገራቸው ሥራ በላይ ሊሠራና ሊደረግ የሚገባ ምንም አንገብጋቢ፣ አስቸኳይ እና ዋጋ ያለው ነገር የለም። ይህም ሥራ የኀጢአት ይቅርታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዓለም እንደተሰጠ የሚናገረውን መልካም ዜና ለሰው ሁሉ ማወጅ ነው።
ጆን ፓይፐር በአንድ ወቅት በጎስፕል ኮአሊሽን ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ከተናገሩት ንግግር ልዋስ፦ “ሲኦል እንዳለ እና ከዚህ ሕይወት በኋላ ወንጌልን ላላመኑ ሁሉ ማብቅያ የሌለው ስቃይ እንዳለ የምታምን ከሆነ በወንጌል ላይ እንዴት ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ? ያንን በእውነት ካመንክ ወንጌልን ለመስበክ ማቆም እጅግ ከባድ ይሆንብሃል” ብለዋል። ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው እና የሚገቡ ብዙ መልካም ነገሮች አሉ። ነገር ግን ሲኦል እውነት ከሆነ በአእምሮአችን ሰሌዳ ላይ በደማቁ ልንጽፈው የሚገባ፣ የሚገባ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ልናስታውሰው አስገዳጅ የሆነ አንድ እውነት አለ። ይህም ሌሎች ሰዎች ፈጽሞ ሊያደርጉት የማይችሉት፣ ክርስትያኖች ብቻ እና ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት አንድ ነገር. . . እንዴት ሰዎች ከኀጢአታቸው ይቅርታ ሊያገኙ እንደሚችሉና ለዘላለም በሲኦል ከመሰቃየት ሊያመልጡ እንደሚችሉ መናገር ነው። ክርስትያን ያልሆኑ ሰዎች ድኾችን መመገብ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማትን መገንባት፣ የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈር፣ የሥነ ልቦና ምክር መስጠት እና የመሳሰሉትን በጎ ምግባራት ሊያደርጉ ይችላሉ። ወንጌልን ለሚጠፉ ሰዎች መመስክርንና የሕይወትን መንገድ ማሳየት ግን ክርስቲያኖች ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው።
መደምደሚያ
ትምህርተ ሲኦል አጅግ አስፈሪና አሰቃቂ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። አስተምህሮው አስፈሪ የሆነው ደግሞ እውነታው አስፈሪ በመሆኑ ነው። ነገር ግን ይህ አስፈሪነቱ ዐይናችንን አዙረን እንዳላየ እንድንሆን፣ ጆሯችንን ደፍነን “ጆሮ ዳባ ልበስ” እንድንለው፣ አልያም ደግሞ ከናካቴው እንድንቃወመውና እንድንክደው በቂ ምክንያት አይሆንም።
በስብከቶቻቸው ውስጥ ትምህርተ ሲኦልን ተቃውመው ሲኦል እንደሌለ በተናገሩና ወይም እንዲሁ አድበስብሰው አጽንኦት ሳይሰጡት ባለፉ ጊዜ እግዚአብሔርን ይበልጥ እንዳከበሩ አና አፍቃሪነቱን ይበልጥ እንደገለጹ የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች በዙሪያችን አሉ፤ ነገር ግን እጅግ ተሳስተዋል። በዚህ ድርጊታቸው እያደረጉ ያሉት ነገር፣ ክብርን ሊሰጡት ከሚፈልጉት ከኢየሱስ ክርስቶስ ባለማስተዋል ክብርን መስረቅ ነው። ስለ ሲኦል አጽንኦት ሰጥተው ባልተናገሩ፣ ወይም የሲኦልን እውን መሆን በተቃወሙ ጊዜ ሁሉ፣ “ኢየሱስ አድኖናል፤ ግን ያዳነን ያን ያህል ከከፋ ነገር አይደለም!” እያሉ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እጅግ አሰቃቂ የሆነው እና ልንጠፋበት የነበረው አስፈሪ ቅጣት፣ እጅግ የከበረውን ልንድንበት ያለውን ክብር ከፍ አድርጎ ለማሳየት የሚጠቅም ወሳኝ የወንጌላችን ክፍል ነው። ምን ያህል ከከፋ ጥፋት እንደ ዳንን ስንረዳ፣ ወደ ምን ያህል ታላቅ ክብር እንደ ዳንን በተሻለ መልኩ እናስተውላለን። የሲኦልን አስፈሪነት አጥርተን ባስተዋልን ቁጥር፣ ያንን ሲኦል ለእኛ ሲል የተጋፈጠውንና ያዳነንን ጌታ ሁሌም በሚጨምር ፍቅር፣ ምስጋና እና አምልኮ እንድንቀርበው ያደርገናል።
በግሬግ ጊልበርት
[1] ማሳሰቢያ፦ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሲኦል የሚለው ቃል የሚወክለው፣ የእግዚአብሔር የዘላለም ቁጣ በኀጢአታቸው በሞቱ ሰዎችና ኀጢአትን ባደረጉት ሰይጣንና መላእክቱ ላይ የሚገለጥበትን ስፍራ ነው። በጽሑፉ ውስጥ ሲኦል ለሚለው ቃል የተለየ ሥነ መለኮታዊ ትንታኔ በመስጠት፣ ሲኦል የሚባለው ቦታ ገሃነምና የእሳት ባሕር ተብለው ከሚታወቁት ቦታዎች የተለየ ለመሆኑ ወይም ላለመሆኑ ዝርዘር ማብራሪያ አልቀረበም። ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሲኦል የሚለው ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገሃነም እና የእሳት ባህር ተብለው ከተጠቀሱት ቦታዎች ጋር በተለዋዋጭነት ይውላል። የጽሑፉ ነጥብ፣ ሲኦል በሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ቁጣ ማመልከት ነው።
[2] (ቀ.ኃ.ሥ) የቀደመው ወይንም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትርጉም።
[3] (አ.መ.ት) አዲሱ መደበኛ ትርጉም።